ከአማራ ሕዝባዊ ግንባር የተሰጠ የአቋም መግለጫ
Updated: Aug 29, 2023
አማራን በማጥፋት ሌሎች ኢትዮጵያውያንን በመጨፍለቅ ኢትዮጵያን በትኖ በፍርስራሿ ላይ የታላቋን ትግራይና ኦሮሚያን ሃገረ መንግስት ለማዋለድ የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት ሆኖ በፀደቀ ዘረኛ ሰነድ አማራው ከፖለቲካ ውክልና እንዲገለል፣ ከሃገሪቷ ኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዳይሆን እና የተረጋጋ ማህበራዊ ኑሮ እንዳይኖር ሲደረግ ቆይቷል። የአማራ ህዝብ ለአገርና ወገን ያበረከተውን ጉልህ ታሪክ በተዛባ የሃሰት ትርክት እንደ ወንጀል በመቁጠር ተቋማዊ የሆነ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተካሂዶበታል። እየተካሄደበትም ይገኛል። የግፍና የመከራው አዙሪት ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ደርሶ በወለጋ፣ በመተከል፣ በአርሲ፣ በሻሸመኔና ሌሎችም አካባቢዎች ሲፈፀም የነበረው የጅምላ ጭፍጨፋ፤ ማሳደድና ማፈናቀል አድማሱን አስፍቶ የአማራ ክልል ብለው በጠሩት ቅዬው ደርሷል። በፋኖ ከፍተኛ ምት እየደረሰበትና ሽንፈትን እያስተናገደ የሚገኘው የኦሮሙማ ብልፅግና ጦር እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ በአማራ ሕዝብ ላይ በድሮን፣ በጦር ሄሊኮፕተርና ሜካናይዝድ ጦር የታጀበ ከፍተኛ ጦርነት ከፍቶበታል። በዚህም ወረራና ጦርነት አያሌ ንፁሃንን በጅምላ በመጨፈጨፍና የእምነትና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን፣ የልማት አውታሮችን በማውደም ላይ ይገኛል።
እንደሚታወቀው በተለያየ አካባቢ ለአማራ ሕዝብ ህልውናና ለኢትዮጵያ እንደ አገር መቀጠል ከኦሮሙማው ብልፅግና ፋሽስታዊ አገዛዝ ጦር ሰራዊት ጋር እየተዋደቀ የሚገኘውን ፋኖ በአንድ ዣንጥላ ስር እያሰባሰበና እየመራ የሚገኘው የአማራ ሕዝባዊ ግንባር ለአማራ ሕዝብና ለመላው ኢትዮጵያውያን የሚከተለውን የአቋም መግለጫ ያስተላልፋል፦
1. ከኢትዮጵያ ምድር እንድትጠፋ ሕግ ፀድቆብህ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየተፈፀመብህ የምትገኘው የተከበርከው የአማራ ሕዝብ ሆይ! ህልውናህን ለዘለቄታው ማረጋገጥና ከሌሎች ወገኖችህ ጋር በመሆን ኢትዮጵያን እንደ ሃገር ማስቀጠል የምትችለው ፀረህዝብና ፀረ-ኢትዮጵያ የሆኑ አጥፊ ጠላቶችህን ማሸነፍ ስትችል ብቻ ነው።
2. የአማራ ሕዝባዊ ግንባር ዓላማና ግብ ፀረ-አማራ፤ ፀረ-እምነትና ፀረ-ኢትዮጵያ የሆነውን ፋሽስታዊ የኦሮሙማ ብልፅግና አገዛዝና አጋሮቹን በሕዝባዊ ትግል በማስወገድ ድርጅቶቻቸውን በሕግ በማገድና ወንጀለኞችን ለፍርድ በማቅረብ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ባለቤት የሆነበት የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ነው።
3. ሕዝብን ከመጨፍለቅና ከመጥፋት፣ ኢትዮጵያን ከመፍረስና ኢትዮጵያውያንን አገር አልባ ከመሆን ለመታደግ የአማራ ሕዝባዊ ግንባር በሚያደርገው ሁሉን አቀፍ የህልውና ትግልና አገርን የማስቀጠል ትግል ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ከአማራ ሕዝብ ጎን እንድትሰለፉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
4. “አማራን ትጥቁን ብቻ ሳይሆን ቀበቶውንም እናስፈታለን” በማለት በኢትዮጵያውያን ሀብትና ንብረት የሚተዳደርን መከላከያ በአንድ ጎሳ ቁጥጥር ሥር ካዋለ በኋላ በድሮን፣ በጦር ጀትና ሄሊኮፕተር በማጀብ እንደ ታንክና መሰል ከባድ የጦር መሳሪያዎችን በማስታጠቅ የሶስት ወር ጊዜ በመቁረጥ አማራን እንዲጨፈጭፍ ወደ “አማራ ክልል” የገባው የፋሽስቱ አብይ አህመድ ጦር ከፍተኛ ሽንፈት በማስተናገድ ላይ ይገኛል። የጦር ሰራዊቱ አባላት ደግሞ ከአማራ ህዝብ ጋር ጦርነት የመግጠም ፍላጎት ባለማሳዬት እጅ በመስጠትና በመኮብለል የኦሮሙማ ብልፅግና ጦር እየተፈረካከሰ በአማራ ህዝብ ያላሰለሰ ድጋፍና ወኔ ፋኖ ከፍተኛ ድል እያስመዘገበ መሆኑን ስንገልፅ በከፍተኛ ሞራልና ኩራት ነው።
5. የአማራ ህዝብና መላው አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሆይ! ሽንፈትን እየተጎነጨ የሚገኘው የኦሮሙማ ብልፅግና ፋሽስታዊው አገዛዝ ከሽንፈቱ ለመዳን የአማራን ሕዝባዊ የህልውና ትግል ለማጨናገፍ የተለመዱና ከአሁን በፊት በተደጋጋሚ የከሸፉ አያሌ ሴራዎችን እያግተለተለ ይገኛል፡፡ እነሱም ድርድር፣ ሽምግልናና በሽግግር የአማራ ተወካይ ማቋቋም የሚሉ ናቸው። በተጨማሪም በሌሎች የውጭ የሰላም አስከባሪ ሃይል ስለማስገባት እያስወራ ይገኛል። የአገዛዙ ዋና ዓላማ ግን ጊዜ በመግዛት የአማራን ሕዝብ ለበለጠ ጭፍጨፋ ለመዳረግ ሰፊ ዝግጅት ለማድረግና አጀንዳ ለመስጠት እንደሆነ ደርሰንበታል።
ስለሆነም፥
1ኛ. የአማራ ሕዝባዊ ትግል ቁርጠኛ ግቡ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር በመሆን የዘረኛውን የኦሮሙማ ብልፅግና ፋሽስታዊ አገዛዝ በማሸነፍ አንድነት፣ ሰላም፣ ዲሞክራሲና ፍትህ በጋራ ሃገራችን ላይ ማስፈን ብቻ ስለሆነ በማናቸውም ዓይነት አጀንዳ ወደ ኋላ አይልም። አይታለልም።
2ኛ. ባለፉት 32 ዓመታት በዘር ማጥፋትና አገር በማፍረስ ወንጀል የተሳተፉ፣ ተላላኪና ተባባሪ በመሆን ያገለገሉ ሁሉ ለሕግ የሚቀርቡ ወንጀለኞች እንጂ የመፍትሄ አካሎች መሆን አይችሉም።
3ኛ. ቀድሞ ለትህነግ መራሹ ኢህአዴግ አሁን ለኦሮሙማ መራሹ ብልፅግና የጀርባ አጥንት በመሆን የሚታወቀው ብአዴን አመራሩ በአዲስ አበባና በተለያዩ አካባቢዎች በማድፈጥ ጠቋሚ አስተኳሽና የመረጃ ምንጭ በመሆን እየሰራ ስለሚገኝ የተቋሙን መዋቀራዊ ሰንሰለትና አደረጃጀት መበጣጠስና ማፍረስ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው።
ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የጋራ ሃገራችንን በተባበረ ክንዳችን እናስቀጥላታለን!
አማራው በክንዱ ህልውናውን ያረጋግጣል!
መነሻችን አማራ
መዳረሻችን ኢትዮጵያ!
የአማራ ሕዝባዊ ግንባር
Comments