top of page

የአማራ አእምሯዊ ውድመትና ቀውስ (Intellectual genocide)

Updated: Sep 4, 2023

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የአማራ ሕዝብ ሰብዓዊ እና አእምሯዊ ሀብቶቹን ፣ ማሕበራዊና መንፈሳዊ እሴቶቹን እንዲሁም ሌሎች መገለጫዎቹን ሁሉ እንዲያጣ ያደረጉ አያሌ የአርበኝነት እና የጦርነት ታሪኮችን አሳልፏል። በመካከለኛው ዘመን ውስጥ እንኳ ከምስራቅ የእስላማዊ ኃይል ከሆነው የአዳል ተስፋፊ ጦር ጋር እንዲሁም ቀጥሎ ከመጡት ከባሌ የተነሱ የኦሮሞ ተስፋፊዎች ጋር ለ400 አመታት በጦርነት አሳልፏል። መልከ-ብዙ ውድመትም ደርሶበታል። በአንድ ወቅት በማሕበራዊ ሚድያ በጋዜጠኛ አንሙት አብርሐም ቀርቦ የነበረው ይሕ የአማራ ሰብዓዊ አቅም መዳከም እና ለምን ሰው አጣን!? የሚል ጥያቄ ምንጩ፡ ረጅም መሠረት ያለው የአማራ የፖለቲካ ጭንቅላቶች ውድመት የፈጠረው የፖለቲካ አስተሳሰብ ውርስ ወናነት (gap) ስለመሆኑ ማጤን ተገቢ ነው ይላል። በዚህ ዝግጅታችን የጋዜጠኛውን ምልከታዎች እናጋራችኋለን።


የኢትዮጵያ የመጀመሪያው "regime" የሆነው የዘውድ ስርዓት፡ ምንም እንኳ የአማራ ገዢ መደብ ተብሎ በብሔርተኛ ድርጅቶች ቢፈረጅም፥ ሥርዓቱ በተለያየ መልኩ ለሰብዓዊ እና አእምሯዊ ውድመቶች ምክንያት የሆኑ ክስተቶችን አስተናግዷል። በመጨረሻው ንጉሰነገስት ዘመን በአማራው ላይ የተከፈቱ ጦርነቶች እንኳ፡ ለሰብዓዊ እልቂቶች ምክንያት የነበሩ ናቸው።


➵ከአንቺም ጦርነት እስከ ሰገሌ ጦርነት ከፍተኛ ውድመት ተፈፅሟል።

➵ ከጣሊያን የቅኝ ግዛት ትግል የተረፈው የጎጃም አርሶአደር የአውሮፕላን ድብደባ ተፈፅሞበታል።

➵ ለአገራቸው ሉዓላዊነት የተዋደቁ እንደነበላይ ዘለቀ ያሉ አርበኞች ተገደሉ።

➵ በአገሪቱ ለውጥን የናፈቁ እነ'ግርማሜ ንዋይና መንግስቱ ንዋይን የመሰሉ ሰዎች ተገድለዋል።


ደርግ የተረከባት ኢትዮጵያ: የአማራ ብሔር ጠበቃ ተደርጎ ስም በወጣለት የዘውድ ስርዓት የተፈፀመውን ጥቃት ያስተናገደችዋን ነው። ደርግም ውርሱን ተከትሎ የአማራን ልሒቃንና ጭንቅላቶች ያወደሙ ጥቃቶችን ቀጠለበት። ከተገቢው በላይ የተራዘመው የዘውድ ስርዓት ቅራኔዎችን ለመመለስ በተደረጉት የአቢዮት ንቅናቄዎች ውስጥ ከአማራው የወጡ ምሁራን እና ወጣቶች በአገር ውስጥና በውጭ አገር ታግለዋል። በመፍትሔ ረገድ ደግሞ በኢሕአፓ እና መኢሶን አደረጃጀቶች ውስጥ ገብተው የመሰላቸውን አማራጭ አራምደዋል።


የአቢዮቱን ውጤት የጠለፈው ደርግ፡ ካፒታል ባልፈጠረች አገር ሶሻሊዝም ፣ ሠራተኛ በሌላት አገር የሠራተኞች ፓርቲ፣ በመመስረት የትውልድ ጥፋቱን ጀመረ።

የደርግ በትር የአማራን መዋቅራዊ ቁመና በሚያዛባ የጥፋት እርምጃ እንዴት እንደተፈፀመ እንመልከት። የዚህ ፅሑፍ ትኩረት የደርግ እርምጃ ከአማራው አንፃር ያደረሰውን ጥፋት መዳሰስ በመሆኑ እንጂ በሌሎች ላይ ያደረሰው ጥቃት የማይታበይ ነው። በመሠረቱ ደርግ ማንነት መርጦ ጥቃት ፈፅሟል የሚል መነሻ የያዘ አይደለም። ይልቁንም ያ ሥርዓት እና ሒደቱ ያስከተለውን አማራዊ ውድመት ማሳየት ለአማራው የትግል ትንተና መነሻ ስለሚሆን ነው።

የደርግ አገዛዝ የዘውድ ስርዓቱን ለመበቀልና ለማጥፋት የወሰዳቸው የማጥቃት እርምጃዎች በዋናነት በአማራው ልሒቃን ላይ ያስከተለው ጥፋት ከፍተኛ ነው።

የዘውድ ስርዓቱን ባለሚናዎች የማጥቃት እርምጃዎች በተለይ ከአማራ የሚወለዱ ልሒቃንን እና በሰፊው የአማራ ህዝብ ላይ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት አድርሷል።

ደርግ ከስርዓቱ ባህሪ አኳያ በመሰላቸው መንገድ አገራቸውን ያገለገሉ የፖለቲካ ልሒቃን መካከል በተለምዶ 60ዎቹ የሚባሉትን የኃይለስላሴ ባለስልጣናት ረሸናቸው። ከነዚህ መካከል እነ ፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉን የመሰሉ ትላልቅ የፖለቲካ ስብዕናዎችና ልሒቃን ጠፍተዋል። ቤተዘመዶቻቸው ተሰደዋል።

በቁሳዊ ኃብት ንጥቂያና ጥቃት ረገድ ፣ ደርግ ያወጀው የትርፍ ቤት አዋጅ ፡ ካፒታል ባልፈጠረ ማህበረሰብ ቤት ሰርቶ መኖርን ነውር በማድረግ በመላ አገሪቱ ቤት ንብረቱ የተነጠቀው አማራ ቀላል አይደለም። አንድ ትውልድ ተሻግሮ በቀበሌ ቤትነት የብሔርተኞች መጠቃቀሚያ ሆኖ ቀጥሏል።

በሺህዎች የሚቆጠሩ የአማራ ቤቶች በአዲስአበባ እና በዛሬው ኦሮሚያ ወደመንግስት ይዞታነት ዞረዋል። በመላ አገሪቱ ሲፈፀም የሚበዛው አኃዛዊ መረጃ በአማራው ላይ እንደሚያመዝን ጥያቄ የለውም። ከአማራ ተነጥቆ ለአማራው ብቻ ሳይሆን ለሌላው ብሔር መሰጠቱ እውነት ነው።

አገርና ከተማን ሲመሠርት የኖረው አማራ በላቡ ቤቱን ሠርቶ መኖር ልማዱ ነውና የደርግ በትር አርፎበታል። የፊውዳልና መሳፍንት ቤቶች ተብለው የአባት እዳ ለልጅ ተርፎ የመኖሪያ ቤት ሀብትና ንብረት የተነጠቁት አያሌ ናቸው።

ብሔርተኛ ድርጅቶች በአማራነት እና በገዢ መደብነት የፈረጁት የዘውድ ስርዓቱ ልሒቅ (መሳፍንትና መኳንንት : እስከ ንጉሱ ድረስ) እንዲህ ቢያልቁም ከገዢ መደብ ፍረጃና ፀረ-አማራ ፖለቲካ ያላቀቃቸው አልሆነም። ያ ገዢ መደብ አልቋል ፣ ተበትኗል ፣ ተመቷል፣ እናም "የፖለቲካ እይታችን ይለወጥ" ያለ የብሔር ድርጅት የለም። የኋላ ኋላ ጨቋኝ የተባለውን ህዝብ ምሬት ለመሸፋፈን ገዢ መደብ ተባለ እንጂ ፀረ-አማራነት አልተለወጠም። መሳፍንትና መኳንንቱን ያፈራ ማህፀን ነገም ይደግመዋል ተብሎ ተፈረጀ። ከመሳፍንት ወገን የሚጠቀስ የዘመኑ የአማራ ልሒቅ ለስደትና ጥፋት ተዳረገ።

  • በደርግ ዘመን ቀጥሎ የመጣው "የቀይ ሽብር እርምጃ ደግሞ አያሌ የአማራ ጭንቅላቶችን አጠፋ፣ ሰፊ ሰብዓዊ ውድመት አስከተለ።

የደርግ ፖለቲካ በአማራ ሰብዓዊና ቁሳዊ ሀብት ላይ ያደረሰው ውድመት በዚህ ሳያበቃ ወደለየለት ሰብዓዊ ውድመት ተሸጋግሯል።

ትክክልም ይሁን ስህተት ለአገር ከነበረ ቀናኢነት የተነሳ በኢሕአፓ እና መኢሶን ለለውጥ የተሰለፉ አማራዎች ኋላም በአባልነትና ደጋፊነት የተሠለፉት አያሌ ናቸው። ከሞላ ጎደል የዘመኑ የአማራና የኢትዮጵያ ምርጥ ጭንቅላቶች ናቸው።

አንዳንዶች አንድ ትውልድ አልቆበታል የሚሉት የቀይ ሽብር ነጭ ሽብር ፍጅት: አንዳንዶች ደግሞ አኃዛዊ ገፅታ ሰጥተው ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ህዝብ አልቆበታል በሚሉት የደርግ የፍጅት እርምጃ ከሞላ ጎደል የፖለቲካ ንቃት የነበረው የዘመኑ ልሒቅ ማለቁ ግልፅ ነው።

በዚህ የእልቂት ሒደት የትኛው የማንነት ቡድን የበለጠውን ዋጋ ከፈለ? በየትኛው የሙያ መስክ የነበሩ ወጣቶች አለቁ? ስንት ሰው ተሰደደ?

የአማራ የፖለቲካ ስብዕናዎችና የአስተሳሰብ ውርሶች የተቋረጡት እዚህ ግድም ነው።


አማራ ቤቱ ኦና የሆነው ÷ ስነልቦናዊና ሞራላዊ ስብራት የደረሰበት በዚህና ቀጥሎ በተፈፀሙበት ሰብዓዊ እልቂቶች ነው። የዘመኑ ጭንቅላቶች ተመንጥረው ተጨፈጨፉ።


ከደብረማርቆሱ "ደም መላሽ" እስር ቤት እስከ ሐረሩ ቆሼ ጨለማ ቤት ÷ ከአዲስአበባው ማዕከላዊ እስከ ጎንደሩ ባታ ማጎሪያ ÷ በመላ አገሪቱ ባሉ ማጎሪያ ቤቶች የአማራ ጭንቅላቶች ተጨፈጨፉ። በፀረ-አቢዮትነት ስንቱ ተቀጠፈ!?


የአማራ እናት መውለዷን እየረገመች ልጆቿን ተነጠቀች። የማህበረሰብ የሞራል ስብራት ወልዶ መሳምን አስረገመ። ብዙዎች እግር በመራቸው ተሰደዱ። በመንገድ የአውሬ እራት የሆኑትን ቤቱ ይቁጠራቸው። የት እንደሆኑ እንኳ ባልታወቁበት ከጥይት የተረፉ የአማራ ጭንቅላቶች በሰው አገር ተሰደዱ። ወልዶ መሳም ይቅርና አልቅሶ መቅበር ለአማራ እናቶች ብርቅ ሆነ።

እንዲህ ሆኖ አማራዎች ለአገር እየታገሉ ሲያልቁ : ጥቂት ብሔርተኞች የዘመኑ የፖለቲካ ልሒቃኖቻቸው በትጥቅ ትግል ተደብቀው የ20ኛውን ክፍለ ዘመን የሚወስኑበትን እድል አገኙ።


ቢኖሩ ለአማራ ጥቅም ሊቆሙ ይችሉ የነበሩ አማራዎች ግን ተጨፍጭፈው አለቁ። የነሌንጮ ለታ እና ስብሐት ነጋ እኩያ አማራዎች አገሬ ሲሉ የትም ቀሩ። እነዚህኞቹ ዛሬም የትውልዱን ፖለቲካ ለመወሰን ከመስራት አልቦዘኑም።

እንዲህም ሆኖ የአማራ ልሒቃን ፍጅት አልተቋረጠም።

  • በዘመነ-ደርግ ሌላኛው የእልቂት ድግስ በብሔራዊ ዘመቻ ቀጠለ !!

በደርግ ዘመን የአማራን ቁሳዊና ሰብዓዊ ሀብት የጨረሰው ፖለቲካ በዚህ አላበቃም። በየአቅጣጫው የተነሱት የብሔር ታጣቂ ቡድኖች በራሳቸው ደግሞ አማራ ጠላት አድርገው ተነሱ። ከኤርትራው ሻዕቢያ እስከ ኦሮሞው ኦነግ : ከትግሬው ህወሓት እስከ ደርግ የአማራን ሰብዓዊ ውድመት የሚያፋጥን የጠላት አስተሳሰብና ተግባር ውስጥ ገቡ።

ደርግ ሁሉም ነገር ወደጦር ግንባር ባለበት ዘመን "ከፀረ-ፊውዳል" እርምጃው የተረፈውን ÷ "ከፀረ-አቢዮት" ፍጅት የቀረውን ÷ ከስደትና መንከራተት የተረፈውን አማራ ወደማያባራ ጦርነት ማገደው።


በልቶ ማደር የቸገረው ወጣት ከእናቱ እቅፍ እየተለቀመ በግዳጅ ወደማያምንበት ወይም ወደ ማይፈልገው ጦርነት ተማግዷል፡፡

ወልዶ ማሳደግ የተረገመበት፡ ወላጅ በልጁ አካላዊ እድገት የተሳቀቀበት ዘመን ሆነ! ፡፡

ስንቱ ወጣት አመለጠ፡ ተደበቀ፡ ሲሸሽ ያዝነው ተብሎ 'የእናት ጡት ነካሽ" እየተባለ የጥይት እራት ሆነ፡፡

በእናት አገር ጥሪ ስም የአማራ ወጣት ከገጠር እስከ ከተማ በአቢዮት ጠባቂ እየታደነ : እናት ልጅሽን ከተደበቀበት አምጪ እየተባለች ተሰቃየች÷ በግዳጅ ታንቆ ለሻዕቢያና ህወሓት ጥይት ተማገደ።


ይባስ ብሎ በወታደራዊ ማሰልጠኛዎች ከአገሪቱ የተለያየ አካባቢ የሚመጡ እና አማርኛ በደንብ የማይችሉት ስልጠናው ላይ "በወታደራዊ ቋንቋ መግባባት አልቻልንም" ተብሎ አማርኛ የሚናገር ወጣት ይምጣልን ተባለ። እናም ከአማራ በብዛት እየታደነ ወደጦር ሜዳ ተዳረገ።

አዎ: ደርግ የአማራን ወጣቶች በአረንጓዴ ካኪ እየጠቀለለ ወደሞት መንደር ወረወራቸው!


የአገር ሉዓላዊነት ጦርነት ቢሆን ቀስቃሽ ሳይፈልግ በጦርነት አውድማ የሚዋደቀው አማራ ፥ በአገር ውስጥ የርስ በርስ ጦርነት ያለፍላጎቱና ሳያምንበት እየታፈሰ ወደ ግንባር ተላከ፡፡ የድርጊቱ ተቃርኖ አልገባ ያለው ደርግ ከመንደሩ እስከ ስልጠና ማዕከል፡ ከስልጠናም እስከ ጦር ሜዳ የሚሸሸውን ኃይል ተሳለቀበት፡፡

በደርግ እየታፈሠ ግንባር የተላከ ኃይል ፡ ከደርግ መውደቅ በኻላ አሁንም ድረስ ከወያኔዎች የተረፈው ስም "ምርኮኛ" መባል ነው፡፡

ባላመነበት ጦርነት፡ ከመንደሩ እየታነቀ፡ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ያለመዋጋት አማራጭ የወሠደን ወጣት፡ የደርግ አሸናፊ ኃይሎች የአማራ ብሔራዊ መገለጫ አስመስለው በተማራኪነት ለማሸማቀቅ ሲጥሩ ይታያል፡፡

ጦርነት አሳማኝ cause ይፈልጋል፡፡ ቢያንስ በሉዓላዊነት ጉዳይ ባድማና ሽራሮ ላይ ለመዋደቅ ከእናት ጓዳ መታነቅ አላስፈለገውም፡፡ "ከእናት አባት ሽሮ ፡ ይሻላል ሽራሮ" እያለ በወኔ ዘምቷል፡ ተዋድቋል፡፡ የዚህ ጦርነት ጀብዱና ሚናው ሳይሆን የደርግ የአፈና ዘመቻ ክንውን የጦር ሜዳ ውሎ ብቃቱ መለኪያ ይደረጋል፡፡

ደርግ፥ "ከወንበዴዎች" ወገናችሁ እያለ ያሰቃያቸው ብዙ ናቸው። የሓሙሲት፡ የበለሳ፡ የሰቆጣ አካባቢዎች ሁሉ የኃይለስላሴን የጎጃም እርምጃ ውርስ ተቀብለው በደርግ የአየር ደብደባ ተፈፀመባቸው።


አማራ እንዲህ በህይወቱም በክብሩም ተዋረደ።

ህወሓት እና ሻዕቢያ በጦርነቱ 60,000 ሰው ሞተብን : መቶ ሺህ ህዝብ አካሉ ጎደለብን እያሉ ስለማቋቋሚያ በጀትና ስራ ሲያወሱ ይሰማል።

ለአገራዊ ግዴታ ተብሎ ዋጋ የከፈለው አማራ ግን ስሙን የሚያነሳውም የለም። ስንት እንደሞተ ስንት አካሉ እንደጎደለ እንኳ የሚናገር የለም። ይባሱኑ በግንቦት 20 'የአሸናፊዎች' ድግስ የአማራ እናቶች ቁስል ይቀሰቀሳል። አዎ ! ደርግ ከአርሶአደሩ ልጅ እስከ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ድረስ የአማራን ሰብዓዊ ኃይል በጦር ሜዳም ፈጅቶታል: አስፈጅቶታል።


ሌሎች የዚያ ዘመን የአማራው ሰብዓዊ እልቂቶችን እንመልከታቸው።


ከዘውድ ቤተሰብ እና የቀይ ሽብር ጦርነት የተረፈው አማራ በደርግ ስልጣን ማግስት የቀረበለት የሞት ድግስ ከሱማሊያ የዚያድ ባሬ ጦርነት ነው። ስንቱ አማራ ዋጋ እንደከፈለ ካራማራ ትመስክር።

የ1966 ዓ ም ድርቅና ርሃብ 250ሺህ ህዝብ ሲሞት አብዛኛው አማራ ነው።

በደርግ አገዛዝ 750ሺህ ህዝብ ያለቀበት የ1977 ርሃብ የፈጀው ዋነኛው ህዝብ የወሎ አማራ ነው፡፡

አማራጭ አጥቶ ከቀየው እየታፈሰ በሰፈራ የተበተነ ህዝብ ዋናው አማራ ነው፡፡

ከሶማሊ እስከ ቤኒሻንጉል ደርግ አማራውንና ትግሬውን ከቀየው እየጫነ አጓጉዞ አስፍሯል፡፡

"ደርግ ውግዘት ይግባውና" ፡ ይሄው ዛሬ ፡ አማራው ከሄደበት ሁሉ በመጤነት እየተገደለ እና እየተሠደደ ይገኛል፡፡


አሳጥሮ ለማጠቃለል: ደርግ ከዘውዱ የተረከበውን ፍጅት በእጥፍ አስቀጠለው። መሳፍንቱንና የዘውድ አካል ያለውን ሁሉ ከህይወት እስከ ንብረት አጠቃው። በውርስ አዋጅ በላቡ የሰራውን ቤት ነጠቀው። በቀይ ሽብር አንድ ትውልድ የአማራ ጭንቅላቶችን አጠፋ። እኩሉን ከአገር አሰደደ። የቀረውን በ17 አመት የሻዕቢያና ህወሓት ጦርነት በግድ ማግዶ ፈጀው። አማራ ሰው ያለቀበት በዚህ መሠል ታሪካዊ ሒደት ነው።


ደርግ እንዲህ ካደረገ በኋላ ደግሞ ይህንን ውርሱን ለ1983 አሸናፊዎች አሳልፎ በመስጠት ተጠናክሮ ቀጠለ።

እንዲህ ከዘውድ እስከ ወታደራዊ ኃይል የአማራ ሰብዓዊና ቁሳዊ ሀብት ተቀጥቅጦ በወደመበትም የብሔር ድርጅቶች አማራን ጠላት ማድረጋቸውን አልተውምና የደርግን ውርስ ቀጠሉበት።


የአማራ ሰብዓዊ እና አእምሯዊ ውድመት : በዘመነ ኢህአዴግም የአማራ ሰብዓዊ እልቂትና የአማራ ጭንቅላቶች ውድመት የዞረ ድምር ቅጥያ ሆኖ : የቀደመው ጥፋት በፈጠረው ምቹ ሁኔታ ቀጠለ።


አሳዛኙ ነገር የሚጀምረው ከደርግ ውድቀት ማግስት ነው። ቅድመ- 83 የተወሰዱት የአማራ አእምሮዊ ሀብት ውድመት በደርግ ውድቀት ማግስት : የአማራ ጉዳይ ጉዳዬ ነው ብሎ የሚደራጅና ወክሎ የሚቀርብ ሰብዓዊ ቡድን እንዲታጣ ነው ያደረገው።

የቅድመ - 83 አማራ ተኮር ጥቃቶች ጉልህ መገለጫ ጅማሮ በድህረ-ደርግ የሽግግር ዘመን አማራን የሚመጥኑ ጭንቅላቶች ተደራጅተው የህዝቡን ይሁንታ ይዘው በሽግግሩ መድረክ መገኘት እንዳይችሉ ያደረገ መሆኑ ነው።

ውግዘት አንድ ትውልድ ላወደመው የቀይሽብር ፍጅትና ስደት ÷ እርግማን ለ17 አመቱ የእርስበርስ ጦርነት ይሁንና የአማራ ታዳጊ ጭንቅላቶች ተፈጁ: ተሰደዱ።

በዚህኛው ዘመን የቀጠለው የአማራ ጭንቅላት ውድመት ስነልቦናዊ ÷ ህይወታዊና ቁሳዊ ጥቃቶች የቀጠሉበት ነው።


በህወሓት/ኢህአዴግ ዘመን: የደርግ፡ "አድኃሪና ፀረ-አቢዮተኛ" ፍረጃዎች ፤ "ትምክህት እና ነፍጠኛ" ተብለው ቀጠሉ! የዘመነ ኢሕአዴግ ፀረ-አማራነት የሚለየው ዝም ያለ ስልታዊና መዋቅራዊ ዘር ማጥፋት የተፈፀመበት መሆኑ ነው። ከደርግ በተለየ ፡ የኢሕአዴግ ዘመን የአማራ ጥቃት እሳቤዎች እና ተግባራት በኢትዮጵያ ታሪክ አንድን ህዝብ ታሳቢ ተደርገው የተፈፀሙ መሆናቸው ነው።


ራሱን በአገራዊ ማንነት እና በኢትዮጵያ ጆግራፊያዊ ማንነት የሚገልፀው አማራ፣ "የኢትዮጵያዊነት ካባህን አውልቅ" ተብሎ ስነልቦናዊ ጥቃቱ ቀጠለ። በአገራዊ ማንነት ያደገው ህዝብ ፣ ለክፋት የወረሰው ማንነት ተደርጎ ጠላት እንዲሰማራበት ተሠራ።

"ኢትዮጵያዊ ነኝ የምትለው የጭቆና ውርስ ልታስቀጥል ነው : አማራ ነኝ በል" ተባለ።


በስነልቦና ደረጃ ያለው አወንታዊ የራስ ምልከታ ማህበራዊ ደረጃ ( social class) በትምክህተኛነት ተፈርጆ አጎንብስ ተባለ።

ያሳለፈው የፍጅት ውርስና ጥቃት የጨቋኝነት ተደረገ። በደርግ የብረት ግፍ የተቀበረው ዘውድ : በደርግ "አድኃሪና ፀረ-አቢዮት" እርምጃ በሞትና ስደት የወደመው ፊውዳል በትምክህትና ነፍጠኝነት ፍረጃ ታድሶ ተቀጠቀጠ። በቀይ ሽብርና የ17 አመት ጦርነት በሞትና ስደት የተመታው የአማራ ጭንቅላቶች ውድመት ይባሱኑ በደርግነት ተፈርጆ አገራዊ ስሜቱ እና ሰብዓዊ ስነልቦናው ተወነጀለ።


በሌላ በኩል በአማራነት መደራጀት ወንጀል ሆነ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ አማራነትን ተቀበል ተብሎ የተዘመተውን ያህል በአማራነት መደራጀቱ ደግሞ ስጋት ተደርጎ ተወሰደ።

CIA ከሃያ አመት በፊት ባወጣው ሪፖርት የድህረ-ደርግ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ስጋት የአማራ መደራጀት (Amhara Mobilization) መሆኑን አሰመረ። የኢህአዴግ ፕሮጀክት የሚደናቀፈው በአማራ መሰባሰብ ነው የሚል ክፉ ትምህርት ተላለፈ።

እናም አማራነትን ማቀንቀን እና መደራጀት ደግሞ ተጠላ። ከደርግ ጥይት የተረፉት እነፕሮፌሰር አስራት የመዐሕድን መስርተው መንቀሳቀሳቸው ስጋት ተደርጎ አዲሱ ፍረጃ ተለጥፎባቸው ተሳደዱ። ማህበራዊ መሠረት ሆኗቸዋል የተባለው የሸዋ አማራ አመራርና አባላት ገና በጅምሩ ተሳደዱ። "የትምክህት ማህበራዊ መሠረት" የተባለውን ሸዋ "ለማረም" ከፌደሬሽን ስሪቱ እሰከ ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቃት የሆነው ሁሉ ሰፊ ነው።

ሊቀመንበሩ ፕ/ር አስራትና ጓዶቻቸውም ያንን የCIA ስጋት (የአማራ መደራጀት) አንቀሳቃሽ በመሆናቸው እስር ቤት ተወረወሩ። ይባሱኑ ፕሮፌሰሩ፣ "እስርቤት ሊያመልጡ ሲሉ ተያዙ" በሚልም የእስር ጊዜያቸው እንዲራዘም ሆኖ ከአምስት አመት ተኩል እስር በኋላ እዚያው ታመው ለህክምና ሳይበቁ በመንገድ ሞቱ።


በአንድ በኩል የማደራጀት ስራው እንዲህ ሲዋከብ በሌላ በኩል አማራን በብሔር ማደራጀት ተፈጥሯዊ ስህተት ተደርጎ ዙሪያ መለስ ዘመቻ ተከፈተ።

በዚህ ሁኔታ "የአማራ ፀባይ ማረሚያ" የተባለው ኢህዴን/ብዐዴን የአማራ ወኪል ሁን ተብሎ ቀጠለ።


እናማ የአማራ ፖለቲካዊ መደራጀት በሃምሳ አመታት ውስጥ ሁነኛ አታጋይ ተቋም እና አማራዊ ርዕዮተ-ዓለም መውለድ ተስኖት የሚፈተነው ሰዎቹን የፈጀ አገራዊ አሰና ፀረ-አማራዊ ሥርዓት በመኖሩ ነው።


የአማራ አእምሯዊ ውድመት ቀጥሏል።


ልክ ደርግ ስልሳዎቹን ረሽኖ ዘመኑን እንደጀመረው ኢህአዴግ የቀሩትን ጭንቅላቶች ለስደት የዳረገውን የ40ዎቹን የዩኒቨርሲቲ መምህራን በመንቀል ነው የጀመረው። እነሱ ነን ባይሉ እንኳ : በርካቶቹን አማራ ናቸው ብሎ ያባረራቸው ናቸው።


ግማሽ ክፍዘ የዘለቀ የትውልድ ጥፋትና ፍረጃ ያንገሸገሻቸው አማራዎች ድፍን ሰላሳ አመት በሁሉም አካባቢ ሲነሱ ሲወድቁ በቻሉት ተንቀሳቅሰዋል። ግን በትምክህተኛነት ተመተዋል። ሰሜን ሸዋማ ታንክም ተነድቷል። ደብረብርሃን "ጠባሴ ጫካ" ፡ አያሌ አማራዎች የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መዐሕድ) አባል ተብለው አልቀዋል።


ሌላው ይቅርና በቤተክህነት አገረ-ስብከቶች ውስጥ ዘረኛነትን ፣ የእምነትና ብሔር ፖለቲካ መቀላቀል የተፈፀመው ብዙ ነው። የትምክሕት ምሽግ የተባለችው ቤተእምነትም፡ "አማራነትን እንድታርም" ተልዕኮ ነበራትና ነው ።

ሆኖም በሥርዓቱ ፡ "አመፀኛን ማትነን" በሚል የተገደሉት፣ ለእስር ተዳርገው የማቀቁት፣ ገንዘብ ተሰጥቷቸው አፋችሁን ዝጉ አሊያም ትገደላላችሁ የተባሉት፣ ፓስፖርትና ቪዛ ተዘጋጅቶላቸው፣ ትኬት ተቆርጦላቸው ወደውጭ የተሸኙትም አያሌ ናቸው። "ውጣ አትበለው እንዲወጣ አድርገው'' በስፋት ተተግብሯል።

የዘመነ ኢህአዴግ አማራ ተኮር ጥቃቶች ከደርግና ከዚያ ቀደም ከነበሩት የሚለዩት : አማራን በአማራዊ ማንነቱ ለይተው የተፈፀሙ ማንነት ተኮር ጥቃቶች መሆናቸው ነው። የዚህ አዋላጅ ደግሞ ህወሓት/ትሕነግ ይባላል !!

ከዚህ ታሪክ የተቀዳ ቁጭት ፣ ከዚህ ጥቃት የተወሰደ ትምሕርት ምን ያለ ይሆን!? ከዚህ መሠል ጥቁር የመጥፋት ታሪክ ያልተማረው አማራ ዛሬም በኦሮሞ ብልፅግናዎች ፈላጭ ቆራጭነት ዘመን፣ የአማራው የሰብዓዊ እና አእምሯዊ ውድመት ቀጥሏል።


በቀጣይ ክፍል እንመለከተዋለን።


የኦሮሙማ ብልፅግና ፖለቲካ እና የአማራ አእምሯዊና ሰብዓዊ ውድመት፤

(በቀጣይ ክፍል ይቀርባል)



 

Disclaimer: The opinions expressed in this article are those of the authors. They do not purport to reflect the opinions or views of the Amhara Popular Front ( APF) or its affiliates.

44 views0 comments

Comments


bottom of page