top of page

የአማራ ወታደራዊ አቅሞች ምዝበራ (ክፍል -3)

Writer's picture: ከፋኖ ሽፈራውከፋኖ ሽፈራው

Updated: Sep 4, 2023


ከሽፈራው የሶማው

በዘመነ ትህነግ፣ አማራው ላይ በተካታታይነት የተፈፀመው፣ ከአእምሯዊ እና ስነልቦናዊ ጥቃት የጀመረው፣ ኋላም ብረት በመግፈፍ የተከተለው፣ ውትድርና በማራከስ እና ወታደርን በመፈረጅ ያሰለሰው አማራን ከወታደራዊ ቁምነገሮች የመነጠል ሴራ አልቆመም፡፡ ተቋማዊ አግላይነቶች በወታደራዊ ቋንቋ ፣ በጎሳ ቁጥጥር፣ በህጋዊ እና አገራዊ መገለጫዎች አይነትም የቀጠለ ነበር፡፡


ትናንትን ያወቀ የዛሬን ለመረዳት አይቸግረውምና የአማራን ወታደራዊ አቅሞች የመንጠቅ ደባዎች በተመለከተ የጀመርነውን ተከታታይ ዝግጅት እንቀጥለው፡፡


አግልሎ የመጠቅለል አካሔዶች እና ተቋማዊ አግላይነቶች ሌላኛው ገፅታ የአገሪቱን ተቋም በአማራ ገዳይነት እና አጥቂነት እንዲሳል እስከማድረግ የሔደ ነበር፡፡


ከሆነው ሁሉ ተጨማሪ የአገር መከላከያ ሠራዊት በዘመነኢሕአዴግከአማራውሞትና ግድያ ጋር የሚነሳ ተቋም መሆኑ ተቋሙ ለአማራ ልጆች ባዕድነትን የሚፈጥር ነው።ከደርግ ማግስት አንስቶ ጥያቄና ተቃውሞ ያነሱ የአማራ ወጣቶች ሁሉ በዚያ "የኢሕአዴግ ሠራዊት" ተገድለዋል። በፕ/ር አስራቱ መዐሕድ አባልነትና ደጋፊነት የተከሰሱ ወጣቶች በደብረብርሃን የጠባሴ ጫካ ተቀብረዋል፡፡ጥያቄያቸውምላሽ አጥቶ በአመፅ የተነሱ ወጣቶች ሁሉ "በኢሕአዴግ ሠራዊት" ተገድለዋል።


ከፋኝ ያሉ የአማራ ልጆች "ሽፍታ" እና "አመፀኛ"በሚል ከመገደላቸው በላይ ባዶ እጃቸውን ተሰልፈው ድምፃቸውን ያሰሙ ወጣቶች ላይ መትረጊስ ተኩሶ የሚገድል ተቋም ሆኖ ተሳለ፡፡ የኢትዮጵያ ሳይሆን "የኢሕአዴግ ሠራዊት" ነውና ከባድመ መልስ ምርጫ-97ን ተከትሎ ወታደሩ ከብዙዎች ቤት ሃዘን ጋር የሚጠራ ሆነ። "አግአዚ" የተባለ ኮማንዶ ክፍለጦር በሕዝብ ገዳይነት ተሳለ።


የአማራ ወጣቶች መቃብሮች ላይ ሳይቀር "በአግአዚ የተገደለ" ተብሎ እስከመፃፍ ደረሰ።

የአንድ ፀሃፊን "ያሳደኩት ውሻ ነከሰኝ" አይነት አባባል የሚጠቁም ነው፡፡

‘’Because we fear others we create an institution of violence to protect us, but then we fear the very institution we created for protection’’ [feaver 1996,150]

አማራ የገጠመው ይሕ ነው፡፡ እንደአገር ባለድርሻ ዜጋ ከውጭ እና ከውስጥ አጥቂዎች እንዲጠብቀው ተብሎ ግብር በሚከፍልበት አገር በጀት የተመሠረተ እና የሚመራ ወታደራዊ ተቋም ዜጎችን ያለልዩነት እንዲጠብቅ ተቀዋቁሞ መልሶ አማራው የሚፈራው እና የሚሸሸው እንዲሆን ተሠራ፡፡ እናምከአማራ ወገን ሆኖ በዚህ ተቋም ውስጥ ማገልገል ከገዳይህ ቤት ገብቶ መስራት ተደረጎ እንዲታይ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ከጠላት ኃይል ጋር መሰለፍ ተደረገ፣ በአማራነት ላይ መሸፈትና መክዳት ተደረጎ የሚታይ ተቋም ሆነ።


ወትሮውንም በደርግ መንግስት አስገዳጅ ዘመቻ የተማረረ ማህበረሰብ ፣ ከደርግ መውደቅ በኋላ የትም የተጣለ ሠራዊት ያየ ማህበረሰብ፣ በትሕነግ ከወታደራዊ ሚና የማራቅ መሠሪ ጥቃቶች ተደራራቢ ጥቃት የደረሰበት ማህበረሰብ ፣ ሌሎች ጥቃቶችን የሚከላከልለት ሳይሆን ተባባሪ አጥቂና ገዳዮቹ ያሉበት ተቋም አድርጎ ቢመለከተው አይፈረድም፡፡

ትሕነግ እንደተመኘው ሆኖለት አማራው በፍቅር የሚቀላቀለው ተቋም ሳይሆን መቆየቱ ሊካድ አይችልም፡፡ የአገራዊ የኃይል ሚዛን ስሌት ስትራቴጂካዊና አጠቃላይ ይዘት ተዘንግቶ በአኃዛዊ እንቶፈንቶ እየተሸፈነ ቀጠለ፡፡


ትሕነጋዊ የወታደራዊ ጥቅለላ እና የአንድ ወገን ተቋምነት ግን በአዲስ ወታደራዊ ካፒታል እና ቴክኖሎጂ ቁጥጥርና የበላይነት የቀጠለ ነበር፡፡


ትሕነግ የፖለቲካ ተግዳሮቶች በወታደራዊ የኃይል ብልጫ ሊፈፀሙ እንደማይችሉ ሲያምን ፣የአገሪቱን ወታደራዊና የፀጥታ ተቋማት በይበልጥ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ሙሉ ቁጥጥር እና ተፅእኖ ብልጫ መፍጠሩን ሲያረጋግጥ በወታደራዊ ተቋማት በኩል የትሕነግ አባልና ታማኝ ወታደሮች ወደካፒታል ግንባታና የሃብት እድሎች ማመቻቸት ተገባ፡፡


በመድሎ እና መገፋት የተከፉ የአማራና ኦሮሞ ወታደራዊ መኮንኖች ደግሞ ወይ ተቋሙን መልቀቅ ወይ ከአገር መውጣት አሊያም ስሜታዊ እርምጃ ወስዶ መታሠርና መታፈን ውስጥ ያልፉ ነበር፡፡

የመከላከያና ፀጥታ ዘርፉ ከአንድ ቡድን ቁጥጥር ወደ አንድ ቡድን ወታደራዊ ካፒታሊስቶች ግንባታ ሲገባ ዘርፈ ብዙ መንገዶችንና ስልቶችን በመጠቀም ነው፡፡ በዳንሻ የእርሻ መሬት ስምሪት የተጀመረው ለይቶ የመጥቀም ትግል "በዋጋ ከፍለናል" የነፃ አውጭነት "ማለፊያ ካርድ" ታጅቦ የሚፈፀም ነበር፡፡


እናም የዳንሻው የትሕነግ ሠራዊት ማቋቋም ስራ በአካል ጉዳተኞችና መሰል አደረጃጀቶች የድጎማ ድጋፍ ቀጥሎ ተሠራበት፡፡ የቤኒሻንጉል እና ጋምቤላ እርሻ መሬቶች በልማት ባንክ ብድር ሰጪነት "የነፃ አውጭ ታጋዮች" የዝርፊያ ካፒታል ምንጭ ተደርገው ተሠራባቸው፡፡ የትሕነግ ወታደራዊ ከበርቴዎች ፈላጭ ቆራጭነት [military oligarchy] የተገነባው በዚህ መንገድ ነው፡፡


የትሕነግ ወታደራዊ ኃይል ወደ ካፒታል ግንባታ ሲሠማራ ውስብስቡ ተቋማዊ የጥቅም መድሎ ስራ ልዩልዩ መንገዶችን የሚከተል ነበር፡፡ በሰላም ማስከበር ስምሪት፣ በወታደራዊ አታሼነት ምደባ፣ በኬላ ቁጥጥር ሽፋን በተዘረጋ የኮንትሮባንድ ንግድ፣ በዓለምአቀፍ እና አሕጉር አቀፍ ተቋማት የጥበቃ ስራ ፈቃድ እና ተቀጣሪነት፣ በግል የጥበቃ ድርጅቶች ቢዝነስ ስምሪቶች እና ቅጥር፣ ወዘተ በዋናነት የትሕነግ ወታደራዊ ኃይል ጡረተኞች መጠቀሚያ ተደርገው ተሠርቶባቸዋል፡፡ በትሕነግ ሽፋን ሰጪነት እና ቀጭን የስልክ ትዕዛዝ የኪራይ ምዝበራው ተጠናክሮ ተፈፅሟል፡፡


ይሕ የወታደራዊ እና ፀጥታ ዘርፍ ወታደራዊ ካፒታሊስት አምባገነንነት ወደ ተቋማዊ የኪራይ እደላ እና ኪራይ አደን [rent seeking and rent hunting] ያደገው ደግሞ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እና የብረታብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ተቋማትን መስርቶ በአንድ ወገን አመራር አብላጫ ቁጥጥር ተይዘው የኢትዮጵያውያን የጋራ ሃብት በጥቂት ቡድን አስተዳደር ስር ወድቆ ሲመዘበር ነበር፡፡


እነዚህ ተቋማት በብቸኝነት በሚጠቀልሏቸው የአገሪቱ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንድም የአዲሱ የወያኔ ወጣት ተግባራዊ ትምህርት መለማመጃ፣ ሁለትም የወታደራዊ ከበርቴዎች መፈልፈያ ፕሮጀክት ማዕከላት እንዲሆኑ ያደረገ ነበር፡፡


ትናንትን ያወቀ የዛሬን ለመረዳት ይቻለዋልና እንቀጥል፡፡

ሕወሓት በኢትዮጵያ የዘረጋውን የአንድ ቡድን የኦሊጋርኪ ስርዓት ግንባታ የዳሰሰ ጥናት [The party that consumes the state: the rise of oligarchy in post-1991 Ethiopia: Tefera Negash: 2019] የወታደራዊ ተቋማትን የአንድ ወገን የዝርፊያ ስርዓት በሚገባ የሚያጋልጥ ነው፡፡ በእነዚህ ተቋማት መምጣት አንድም ተቋማቱ የተመሠረቱበትን የልማት ዓላማ ስተው የእዳ ምክንያት የሆኑ ሁለትም በሙስና የተጨማለቁ እንደነበሩ ያትታል፡፡


አገሪቱ በትክክልም ወደ ወታደራዊ ከበርቴዎች ፈላጭቆራጭነት የተሸጋገረችው እነዚህ ተቋማት ከአገራዊ አቅም ገንቢነት ይልቅ የአንድ ብሔር ተወላጅ መክበሪያ እና መማሪያ እንዲሆኑ ተደርገው ሲመዘበሩ ነበሩ፡፡ ይሔ በአገሪቱ የሚፈፅሙት ምዝበራ ከኬላ ኮንትሮባንድ ወደ መርከብ እና አውሮፕላን ኮንትሮባንድ ተቀይሮ አገር ጉድ ያሰኘ ሌብነት የተደመጠበት ነበር፡፡

በሩብ ክፍለዘመን የገዢነት ታሪክ የአገሪቱን መከላከያ ሠራዊት እና የደሕንነት ተቋም ከፍተኛ አመራርነት ከ50 በመቶ በላይ ተቆጣጥሮ የኖረው የትሕነግ አምባገነን ቡድን በአገሪቱ ሠራዊት ውስጥ የውክልና መመጣጠን መኖሩን ለማሳመን ሲታትር እና ስለደርግ ትግል ሲያወሳ የ25 ዓመታት የስልጣን ዘመን ርዝማኔ አያሳፍረውም ነበር፡፡ ልክ የዛሬዎቹ ብዙ ነን ማለትን የቁጥጥር ፈሊ እንዳደረጉት ማለት ነው፡፡


ስለሠራዊት ተመጣጣኝነት እና የሠራዊት አመራር ምደባ አመክንዮ ሲደረድሩ የኖሩት ሰዎች ከ2010 ለውጥ በኋላ ስልጣን ሲነጠቁ የወጣቱንና ውስጣዊ ትግል ውጤትነቱን ለማጣጣል "ባንክም ታንክም በእጃችን እያለ ፈቅደን እንጂ ተገደን ያጣነው ስልጣን የለም" ሲሉ ተደምጧል፡፡ ዘመናቸውን ሁሉ ባንክና ታንክ የአንድ ወገን ለማድረግ መታከታቸውን መመስከራቸው ለአዲስ መረጃነት የማይመጥን የአደባባይ ሐቅ ነው፡፡


ትሕነግ በጥቅምት 24 ፡ 2013 ተግባሩ የገለጠው፡ "የወታደራዊ መለዮ ቅሌት" የዚያ ረጅም ጊዜ የፈጀ ፡ ሌላውን በተለይ አማራውን ትጥቅ የማስፈታት እና ጠቅልሎ የመቆጣጠር አላማዎችን የመጨረሻ እሳቤ በተግባር ያረጋገጠበት ሒደት ነው፡፡


ጥቅምት 24/2013 በብሔር ተደራጅተው በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ የተፈፀመው ግፍ ከላይ ስንመለከተው የቆየነው የአንድ ቡድን የረጅም ጊዜ ስሌት እና ሴራ ቅጥያ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ታሪክ ትሕነግ መራሹ ኃይል ያንሁሉ ወታደራዊ ማግለል እና ማጥቃት ፈፅሞ በብቸኝነት ተቆጣጥሮት ሲኖር፣ ውትድርናን ዝም ብሎ በመድሎ ምዝበራ ወታደራዊ ከበርቴዎች ፈጥሮበት እና ከብሮበት ለማብቃት ብቻ ሳይሆን ፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይል ሚዛን ጨዋታ ውስጥ ዛሬ እንደሚመጣ አውቆ፣ ሲያደርገው የኖረው ሁሉ በቀጣይነት ወታደራዊ ብልጫውን አስጠብቆ ለመኖር የዘረጋው ስርዓት ነበር፡፡


በሠራዊቱ አመራርና አባልነት ውስጥ የነበሩ፣ አገር ሳይሆን ብሔር ብቻ ያላቸው የትግሬ ወታደሮች ተቋማቸውን ከድተው፣ ለአገር ሳይሆን ለቆመላቸው ፓርቲና ብሔር ታምነው የመለዮ ጓዶኞቻቸውን በዘር ለይተው ጨፈጨፉ።


በመለዮ ውስጥ ተደብቆ ለዘመናት የኖረ እና ተኮትኩቶ ያደገ አስተሳሰብ በተግባር የተገለጠበት ነው፡፡

ቁጥጥር እና ብልጫ የተሠራው ለዚሁ ነበር፡፡ በሩብ ክፍለዘመን በሌሎች ላይ በተለይ አማራው ላይ ከሠሩት ወታደራዊ-ማጥቃት በተጨማሪ ብልጫና ቁጥጥር የሰጣቸውን እድል ተጠቅመው በአገሪቱ የፀጥታ ተቋማት ሁሉ በብሔር ተመራርጠው በሕቡዕ ተቧድነው ቀን መርጠው የቀበሮ ጉድጓድ ጓደኞቻቸውን አረዷቸው፡፡


አምነው ጀርባ የሰጧቸውን ከዷቸው፡፡ ቃለ መሃላ የፈፀሙበትን ሰንደቅ አላማ ጥለው ለቡድን ጥቅም ጓዶቻቸውን መቱ፡፡


በዚህ ጥቃትም አማራንመርጠው ጨፈጭፈዋል፣ "ከአማራ ውጭ ከሌሎቻችሁ ፀብ የለንም" እያሉም ለመከፋፈልና በዘር ለማቧደን ሠሩ፡፡ ይሕ አስነዋሪ የወታደራዊ መለዮ ቅሌት በዚህ አገር የፀጥታ እና ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ጥቁር ነጥብ ሆኖ ሲዘከር ይኖራል፡፡ በዚሕች አገር ከዚያ ብሔር ወጥቶ የጋራ ወታደራዊ መለዮ ለብሶ ከሌሎች ጋር የሚሰለፍ ለማግኘነት እና ለማመን ጊዜ መውሰዱ አይቀርም፡፡


Dr. Kristen A. Harkness የተባሉ ምሑር በሠሩት ጥናት (The Ethnic Army and the State: Explaining Coup Traps and the Difficulties of Democratization in Africa) በቅኝ ገዢዎች የክፋት ስሪት የተነሳ የድሕረ-ቅኝ ግዛት አፍሪካዊ ወታደራዊ ተቋማት የዘር መድሎ ባሕል ውርስ የሚያምሳቸው ሆነዋል፡፡ ከነፃነት ማግስት አፍሪካን ያመሱ ወታደራዊ መፍንቅለ መንግስታት ሁሉ መነሻቸው ጎሳን ማዕከል ያደረገ የወታደራዊ ተዓማኒነት ውርስ ነው፡፡

"Throughout colonial Africa, race defined who could be trusted to command. Conceptions of ethnic loyalty also shaped rank-and-file recruitment practices.

Colonial military practices provided a ready model of ensuring loyalty through racial and ethnic manipulations." (2016፡ 9)


የትሕነግ ስራም ከቅኝ ገዚዎቹ የባሰ ዘረኛ ስርዓታዊ ባህልን የተከለ፣ ታማኝነትን በወታደራዊ አዛዦች ብቻ ሳይሆን በእምነት ተቋማት አስተዳደሮች ሳይቀር በብሔር መስፈሪያ ያደረገ የበደል በደል ነው፡፡ ቅኝ ገዢዎቹ ወታደራዊ ታማኝነትን ብሔር እንደመዘኑት ("colonial practices normalized the idea that race and ethnicity were linked to military loyalty") ትሕነግም ያንኑ አድርጓል፡፡


ልዩነቱ የአንድ ወገን ወታደራዊ አዛዦች ጥቅለላ በሌሎች የአፍሪካ አገራት ለተደጋጋሚ መፍንቅለ መንግስት ሲዳርግ በኢትዮጵያ ግን በአንድ ወቅት በእነ አሳምነው ፅጌ የተሞከረውንም ያኮላሸ የፍፁማዊ ወታደራዊ ቁጥጥር ነበር፡፡


የትግራይ ኃይሎች ሲዘጋጁበት እና ሲፈሩት የኖሩትን ጦርነት በብሔር ባደራጁት ጦር ታግዘው የጀመሩት ጦርነት ነበር፡፡ ብቻቸውን ሲሰለጥኑበት ፣ ብቻቸውን አቅም ሲገነቡበት በኖሩት የኢትዮጵያ ወታደራዊ ተቋም ያገኙትን ልምድ ይዘው ፡ ከወታደራዊ ተቋማት ሲያባርሩት እና ሲያገፉት የኖሩትን የአማራና አፋር ሕዝብ በወረራ ይዘው በፈፀሙበት የዘር ማጥፋት የወታደራዊ የበላይነት እና የጦር አዋቂነት ፕሮፖጋንዳ መስማት ለተበዳይ ቢቆጭም ለእነሱ ሃፍረት የሚፈጥር አልሆነም፡፡


በተከታታይ ያቀረብናቸው የትሕነግ ዘመን አማራን ከወታደራዊ አቅም እና ወታደረዊ ሰው ባለቤትነት የመንቀል ሂደቶች ለዛሬ እና ነገ ያላቸው ትርም ኃያል ነው፡፡

ልክ እንደትናንቱ ስልጣን የተቆጣጠረው ኦነጋዊ ኃይል በዘር ማጥፋት እና ዘር ማፅዳት የሚያከናውነውን ፀረ-አማራ እርምጃ ፣ የአማራን ወታደራዊ አቅሞች እና እድሎች በማጥፋት ብቸኛ ተቆጣጣሪነቱን ለማረጋገጥ እየሠራ ነው፡፡


በዚህ ወቅት አማራን ትጥቅ አስፈታለሁ ብሎ ቶርነት በማወጅ መሳሪያን ብቻ ሳይሆን ሊተኩስ የሚል አማራን አጠፋለሁ ብሎ ተነስቷል፡፡

የዚሕን ጠላት ዝርዝር አማራ ተኮር ወታደራዊ ደባዎች እና ትጥቅ አልባ የማድረግ ሴራዎች በቀጣዩ እና በመጫረሻው ክፍል እንቃኛለን፤ ድል ለአማራው ወገናችን፡፡



 

Disclaimer: The opinions expressed in this article are those of the authors. They do not purport to reflect the opinions or views of the Amhara Popular Front ( APF) or its affiliates.






10 views0 comments

Коментарі


bottom of page