top of page

የአማራ ወታደራዊ አቅሞች ምዝበራ (ክፍል -1)

Writer's picture: ከፋኖ ሽፈራውከፋኖ ሽፈራው

Updated: Sep 4, 2023


ከሽፈራው የሶማው


“በዓለም ላይ እንደዚያ ሕዝብ የታጠቀ የለም” የሚለው እና አብይ አሕመድ ለጋዜጠኛ መሳይ መኮንን የተናገረው ንግግር በብዙዎች አእምሮ የሚታወስ ነው፡፡ ጃዋር መሃመድ ከእስር ወቅት በኋላ መጀመሪያ ወደሚድያ በቀረበበት መድረክ “የአማራ ሕዝብ በከፍተኛ ደረጃ ታጥቋል፤ በአስተሳሰብም ሚሊታራይዝድ ሆኗል፤ ስለሆነም ዲ-ሚሊታራይድ የማድረግ ሒደቶች አስፈላጊ ናቸው” ሲል ሰፊ ስጋቱን ተናገረ፡፡ ሌንጮ ለታ እንዲሁ የአማራ መጨፍጨፍ ሳይሆን ራሱን ለማዳን መታጠቅ የፈጠረበትን ስጋት ሳደብቅ ተናግሯል፡፡


አማራ በሌሎች ሲወጋ እና ሲጠቃ ሳይን ራሱን ለመከላከል ሲያስብ የሚጨንቃቸው ሁሉ ከነዚህ እሳቤዎች ውጭ አይደሉም፡፡

የእነዚያ የኦሮሞ ልሒቃን ንግግር ቅጥያ የሆነው አማራን ትጥቅ የማስፈታት እና ወታደራዊ አቅሞቹን የማሟሟት ኦነጋዊ ሴራ ሰፊ መሠረት እና ስልጣን ተኮር ስጋት አዝሎ ፤ ነገር ግን “ህግ ማስከበር” በሚባል የዳቦ ስም ጦርነት ከፍቶ አማራን ለማዳከም የሚፈፀም ጥቃት ነው፡፡


አማራን እረፍት የመንሳት ረጅም ሂደቶች በተለያየ እሳቤ እና ስሌት ተጎንጉነው የሚቋጠሩ የክፋት ስሌቶች ናቸው፡፡ በዘመን ርዝመት ያልተቀየሩ፣ በተዋንያን መለዋወጥ ያልተቋጩ ፀረ-ህዝብ አላማዎች ናቸው፡፡ ይሕንን ጉዳይ ስናነሳ ታሪካዊ መሠረቱን እና በተለያዩ አካላት እና ስርዓቶች ቅብብል የቀጠለ ጥቃት መዳሰስ ተገቢ ነው፡፡


አንድን ህዝብ እረፍት የመንሳት እና በማያቋርጥ የጥቃት አዙሪት ለማንበርከክ ከሚሠሩ ጉዳዮች መካከል ደግሞ የዚያን ህዝብ በወታደራዊ አቅሞች እና ተሳትፎ ማራቆት እንዲሁም በብረት እና በአስተሳሰብ “ትጥቅ ማስፈታት” ነው፡፡

ሁሉም አማራን እናጥቃ ብለው የተነሱ አካላት ሁሉ የዚያንን ሕዝብ ወታደራዊ አቅሞች ለመመዝበር የማይታክቱ መሆናቸው ነው፡፡


የአማራን ወታደራዊ ተሳትፎ፣ ወታደራዊ አመራር ሰጪነት በአጠቃላይ አማራን ከወታደራዊአቅምና ተቋም ለመነጠል መስራት ነው፡፡ ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመግዛት በመጣ ጊዜ ያደረገው ሙከራ ይሕ ነበር፡፡ ዳሩ ባይሳካለትም፡፡

ትግራይ በቀሉ ትሕነግ ደግሞ ሆን ብሎ አማራን ትጥቅ ለማስፈታት በስልት የሠራቸው ክፋቶች ለዛሬው አማራ ተኮር ጥቃት እና ለቀጠለው እልቂት ትልቅ ሚና ያለው በመሆኑ በልዩ ትኩረት መረዳት ከሚጠይቁት አማራ ተኮር ጥቃቶች መካከል ነው።


በአማራው ወታደራዊ አቅሞች እና እድሎች ላይ ጥቃት ፈፅሟል ስንል በዋናነት የአማራውን የአርበኝነትና ጀግንነት ስነልቦና ለማዳከም፣ ከወታደራዊ ተሳትፎ በማግለልና በመግፋት፣ አማራው ወታደራዊ አመራሮችና አርኣያዎች እንዳይኖሩት በማድረግ፣ የመጪ ዘመናት አማራዊ ወታደራዊ አቅሞች እና ተቋሞች እንዳይኖሩት ሰፊ ደባ ፈፅሟል ማለታችን ነው፡፡


ይሕ ደባ ግን ዛሬም በኦሮሞ ልሒቃን ዘመን ተባብሶ የቀጠለ አማራ ተኮር የጥቃት መስክ በመሆኑ ጉዳዩን በጥልቀት እና በተከታታይ ልንመለከተው ወደናልና አብራችሁን ሁኑ፡፡


የተለያዩ የማንነት ቡድኖችና ፍላጎቶች በሚኖሩበት አገር ውስጥ እንደሌሎች ተቋማት ሁሉ የወታደራዊና ፀጥታ ተቋማት ይዘትና ቅርፅ የአገሪቱን ሕዝብና ፍላጎቶች ሊመስሉ የግድ ነው፡፡

የኃይልና ስልጣን ግንኙነት ባልተገራበት ማሕበረሰብ ውስጥ የስልጣን ዋስትና የኃይል ቁጥጥር ብልጫ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ስልጣን በሕዝብ ይሁንታ ሳይሆን በኃይል ብልጫ የሚጠበቅ ይሆናልና ሌላውን አዳክሞ የራስን ጉልበት በማፈርጠም የሚገነባ የስልጣን ቁጥጥር ነው፡፡ ከረጅም ጊዜ አኳያ ሲታይ ግን የኃይል ሚዛን መዛባቱ ፉክክርን ስለሚያስከትል ግጭትን ይወልዳል፡፡


ፍራንሲስ ፉክያማ (2018) በሶሪያ የበሽር አል-አላሳድ ቤተሰብ ያችን አገር ለረጅም አመታት የገዛበትን መንስኤ ሲያነሳ የሚጠቁመን ይሔንን የጉልበት ቁጥጥር የስልጣን ምንጭ የማድረግ አካሔድ ነው፡፡

የሶሪያን ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ከአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1970ዎቹ ጀምሮ ተቆጣጥሮ የመኖሩ መነሻ በፈረንሳይ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ወቅት 12 በመቶ የማይበልጡት የአላሳድ ጎሳ የሆኖኑት አላዊቶች (Alawites) ከፍተኛ ወታደራዊ ተሳትፎ እና ቁጥጥር ስለነበራቸው ለድሕረ-ቅኝ ግዛት የኃይል ብልጫ እንዳገዛቸው አንስቷል፡፡ "ስልጣን በኃይል ይፀናል" ነውና ያለፉትን ከ50 ዓመታት በላይ በፈርጣማ ወታደራዊ ጫና አባት እና ልጅ የሚዘውሯት ሶሪያ ዛሬም ከነመከራዋ አለች፡፡


ልክ በተለያዩ አገራት በሕዝብ ብዛታቸው እና ፖለቲካዊ አቅማቸው አነስተኛ የሆኑ ቡድኖች በወታደራዊ ቁጥጥር ብልጫ ስልጣን አስጠብቀው ለመኖር እንደሞከሩት ትሕነግም የወታደራዊ እና የመረጃ ተቋማትን በብቸኝነት ተቆጣጥሮ የስልጣን ጥቅሙን በዘላቂ የኃይል ብልጫ ለማስጠበቅ ዘልቆ ያልዘለቀ ግን ቀላል የማይባል ጥቃት ያደረሰ ጥረት አድርጓል፡፡

"ስልጣን ያለኃይል ብልጫ አይፀናም" ይሉት ብሒል ስላለ ብቻ ሳይሆን፤ ትሕነግ እንደአንድ አምባገነን ኃይል ከደርግ ውድቀት ማግስት ራሱን በአሸናፊነት የሚመለከት ስለሆነ ስልጣን ለማደላደል እና ለመጠበቅ የሚያግዙ የወታደራዊ፣ የደህንነት እና የውጭ ጉዳይ ተቋማትን "የአሸናፊ ኃይል ተገቢ ይዞታዎች" አድርጎም የሚመለከት ስለነበረ ነው፡፡

ትሕነግ/ሕወሓት በኢትዮጵያ ፖለቲካ-ኢኮኖሚ ውስጥ ለምን እና እንዴት ለ27 ዓመታት ብልጫ እና ቁጥጥር ይዞ ኖረ? ብሎ የሚጠይቅ ካለ ከወታደራዊ ኃይል ሚዛን እና ቁጥጥር ብልጫው እና ቁንጥጫው የተነሳ በሌላው ፖለቲካዊ አመራር ላይ ያደረ ስጋት እና ፍርሃት በዋነኛነት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች አንዱ ሆኖ ይገኛል፡፡ የፖለቲካዊ ብልጫ ጫናዎች ሚና እንዳለ ሆኖ የኃይልና ጉልበት ሚዛን መዛባቱ ዋነኛው ነው፡፡


የስልጣን እና ቁጥጥር ምንጭ ኃይል ሲሆን፡ የራስን የኃይል ምንጭ አማራጮች እና ቁጥጥር ማሳደግ ብቻ ሳይሆን የተቀናቃኝን እና ከኃይል አማራጭ ውስጥ ስጋት የሚደረግን አካል የኃይል አቅም እና አማራጮች ማዳከም የጨዋታው ሕግ አካል ተደርጎ ይሠራበታል፡፡


በዚህ ሒደት ትሕነግ ሰፊ አገራዊ ተዓማኒነትን ከአርበኝነት ጋር ያዛመደውን አማራ፤ በጠላትነት የፈረጀውን አማራ፣ በኢትዮጵያ ትርጉም የሌለው የተበተነ ኃይል እንዲሆን የፈለገውን አማራ ከርክሞ ተፅዕኖ የሌለው አካል ለማድረግ ብዙ ለፍቷል፡፡ በዚህ ረገድ የአማራን የኃይል አማራጭ የሚያቀጭጩ እና ወታደራዊ አቅሞቹን የሚያሟሙ እርምጃዎች በመውሰድ፣ ከወታደራዊ እሳቤና ተሳትፎ በማፋታት፣ የኃይል ሚዛኑን ማዛባት እና የኃይል አማራጭ እድሎቹን ለመዝጋት በተጠና መልኩ ተመጋጋቢ የማጥቂያ ስልቶችን ፈፅሟል፡፡


1) የአማራውን የወታደራዊ ስነልቦና እና ታሪክ መትቶ "ትጥቅ ማስፈታት"


በትሕነግ አማራ ተኮር ወታደራዊ ትጥቅ ማስፈታት ጥቃት ውስጥ ቀዳሚው ነገር የአማራውን አስተሳሰባዊ እና ስነልቦናዊ ስሪት የጥቃት ማዕከል ማድረግ ነው፡፡ ይሔውም የአማራን ወታደራዊ ባህል፣ የጀግንነትና አርበኝት አስተሳሰብ እና እሴቶቹን አዳክሞ "ትጥቅ የማስፈታት" ተግባር ነው፡፡

ስነልቦናዊ ጥቃትና መሸማቀቅ በመፍጠር “የአስተሳሰብ ትጥቅ ማስፈታት” (በሙያተኞች አጠራር mental dimilitarizaton) ነው፡፡

የአማራ የአርበኝነትና ጀግንነት እሴትና ስነልቦና በድልም ይሁን በጥቃት ጊዜ፣ በደስታም ይሁን በሃዘን ስሜቱን የሚገልፅበት ባህል ነው፡፡ አማራ ይፎክራል፣ ያቅራራል፣ ይሸልላል፣ ያፏጫል፣ ያንጎራጉራል፣ ወዘተ .. አርበኝነቱን፣ አልነካም ባይነቱን፣ ጀብዱውንና ጀግንነቱን መግለጫ እሴቱ ነው፡፡ ፉከራ፣ ቀረርቶና ሽለላ ጀግናን ማድነቂያው፣ ማደፋፈሪያው፣ መጨከኛው፣ መውቀሻና ቁጭት መፍጠሪያው ነው፡፡

ጸረ-አማራው የትግራዩ ትሕነግ ግን ከአንድ ሕዝብ መገለጫ ባሕልነት ይልቅ "ትምክህተኛነት" እና "የወደቀ ጨቋኝ ስርዓት መገለጫ" አድርጎ ሲያነውረው ኖረ።

መለስ ዜናዊ የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት በገመገመበት ፅሁፉ፤ "በጦርነቱ ከደርግ ጋር የተቀበረው ፉከራና ቀረርቶ ከመቃብር ተነስቶ መስተጋባት ጀመረ" በሚል የዚያ ጦርነት ሒደት ኃጥያት መገለጫ፣ ፉከራና ቀረርቶ ለአገር ሉዓላዊነት ቅስቀሳ ውለው መታየታቸው መሆኑን አሳየ፡፡

ይሕ አማራውን በስነልቦና ትጥቅ የማስፈታት ትሕነጋዊ ሴራ አንዱ መገለጫ ነው!


በሌላ በኩል ደግሞ ፍረጃ እና ማጥላላት የአማራ ትጥቅ ማስፈቻ ስልቶች ተደርገው ተሠርቶባቸዋል፡፡


ትሕነግ 17 ዓመታት በፈጀ የነፍጥ ትግል ስልጣን ይዞ፣ ስልጣኑንም በነፍጥ አንጋች ሠራዊቱ እየጠበቀ በኖረበት ፡ አማራውን "ነፍጠኛ" በሚል አሉታዊነት አላብሶና ፈርጆ ባቀረበው ትርጉም ፡ አማራውን "በብረትነካሽነት" ሊፈርጀውናሊያሸማቅቀውታግሏል።

"ጦርነት መንግስታትን ፈጠረ ፣ መንግስታትም ጦርነትን ፈጠሩ" የሚለው ዓለምአቀፍ የመንግስታት ምስረታ ታሪካዊ ሒደቶች ጠፍቶበት ሳይሆን፣ የተከለው ከፋፋይ ፖለቲካ እና የሁለት አገረ-መንግስት እሳቤው ስጋት የአገር ወዳዱን አማራ አድርጎ በማሰቡ ነው፡፡ የአማራን ወታደራዊ አቅም ለማዳከም ያደረገው የስነልቦናዊ ጥቃት አካል ነው፡፡ የአፄ ምኒልክ መንገድ፡ ከጣሊያኑ ጋሪባልዲ ወይ ከጀርመኑ ቢስማርክ በምን እንደሚለይ አይናገርም፡፡

በኢትዮጵያ ረጅምና ያልተነጣጠለ የመንግስትነት ታሪክ ውስጥ፤ አገር የተጠበቀበት አርበኝነት፣ የአገር ታማኝነትና ጀግንነት ታሪኮች የወታደራዊ ውርስ እሴቶች እንዳይሆኑ በአማራ ጭቆና ስሑት ትርክት ቀይሮ አነወራቸው፡፡

የመካከለኛው ዘመን ረጅም የመንግስት ምስረታ ሂደቶች በጦርነት ሒደቶች ተፈፅመው እንደታሪክ ካበረከቱት ቁምነገር ይልቅ የአማራ ነገስታት ብቸኛ ታሪክ አድርጎ ስለሚያያቸው፣ በጨለማ ዘመንነት ፈረጃቸው፡፡

"ፋኖነት" የአገር ታማኝነት እሴት፤ የአርበኝነት ሕያው አደረጃጀትና ስልት መሆኑን በመካድ የቀድሞ ስርዓት መገለጫ ብረት ነካሽነት ለማድረግ ሠራ፡፡ “ፋኖ ተሰማራ” ማለት ያለፈበት ብቻ ሳይሆን የማይጠቅም ጉዳይ አድርጎ ሊሠራበት ታትሯል፡፡

የሰለጠነ ሲቪክ ፖለቲካ በነጠፈበትና የኃይል ሚዛን የሥልጣን እድሜ ዋስትና በሆነበት ክፍለዓለም፣ ትሕነግ ሁሌም የሚጠረጥረውን አማራ ታሪክና አርበኝነት ፣ ወታደራዊ ባህል እና እሴት በማጥቃት በስነልቦና የመስለብ እና ትዝታ የመንጠቅ አላማውን እሴቶችን እና ባህሉን በማንቋሸሽ እና በማጣጣል ሰራበት፡፡

ከደርግ መውደቅ ማግስት ስልጣን ሲቆጠጠርም በመላው አማራ የጦር መሳሪያ በማስወረድ ከወታደራዊ አማራጭ ነፃ የሆነን አማራ ለመፍጠር ሠራበት፡፡

በዚህ ሳያበቃ፡ በኢሕዴን/ብአዴን መታሰቢያ ሲገነባጠበንጃ ዘቅዝቆ ያጎነበሰ አማራ ሐውልት በማቆም የትጥቅ ማስፈታት ጥረቱን በሐውልት ወከለው፡፡ ለ27 ዐመታት በዘለቀው የትግራይ ሚድያ ግን ያልተቋረጠ ወታደራዊ ጀብዱ ተረክ እና የጦርነት አሸናፊነት ስነልቦና ግንባታ ይከናወን ነበር፡፡

ትሕነጋውያን፤ ወታደር ማለት ደርግን ያሸነፈ፣ ወታደራዊ ታሪክና ሳይንስ ማለት ለ17 ዓመታት የተደረገ አስመሰለው ይተርኩት ነበር፡፡ የአማራንአርበኝነትና ጀግንነት ጠበንጃውን ዘቅዝቆ የትግሬን የአሸናፊነት ትርክትና ሰበካ እያዳመጠ እንዲኖር ለማድረግ ሠራ፡፡ በልዩ ወታደራዊ አቅም ባለቤትነት ሰፊ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለእነሱ ጦርነት አዋቂ እንደሌለ አድርጎ እንዲያስብ አድርገውታል፡፡


2) ወታደርነትን አራክሶ ማግለል፡ አግልሎ መጠቅለል


በየትኛውም አገር የድሕረ-ጦርነት ሁኔታ ላይ እንደሚታየው፣ ሠራዊትን ወደ ሲቪል ማሕበረሰብ መልሶ የማደራጀትና የማቀናጀት ስራ ትልቅ የሰላም ግንባታ መንገድ ነው፡፡ አያሌ በጎ አሳቢ የሰላምና ዲሞክራሲ ተቋማት፡ ከፍተኛ ሃብት የሚያፈሱበት ቁምነገር ነው፡፡


ደርግን የተካው ትሕነግ መራሹ መንግስት ከዚህ አኳያ ድህረ-1983 ያደረጋቸውን እርምጃዎች ከአማራ ትጥቅ የማስፈታት (ዲሚሊታራይዜሽን) ግቦቹ አኳያ በሶስት ከፍሎ መመልከት ይቻላል፡፡

የቀድሞ ሠራዊትን ውትድርና ማራከስ ፣ አማራውን ከወታደራዊ ተቋማት ማግለል እና ወታደራዊ ተቋማትን በብቸኝነት የመጠቅለል ስራዎች ናቸው፡፡


የቀድሞ ሠራዊትን ውትድርና ማራከስ በተመለከተ ያደረገው የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሠራዊት የነበረውን ጦር በትኖ በማደኸየት ራሱን እና የነበረበትን ውትድርና የማራከስ ተግባራት ናቸው፡፡

የደርግ መንግስት ከወደቀ በኋላ፣ የአገሪቱን ጦር የመልሶ ማቋቋም ጉዳይ፣ "ተሸነፈ" የተባለው ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ የአገሪቱ ሠራዊት ሳይሆን "ድል አድራጊ" የተባለው የትሕነግ/ኢህአዴግ ሠራዊት ዋነኛ መጠቀሚያ ሆነ፡፡ የጦር መልሶ ማቋቋም ድጋፎች በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች እና የጦርነት መልሶ ማቋቋም በሚል ወደ ትግራይ የሚመለከቱ ነበሩ፡፡


የጦር ጉዳተኞች ድጋፍ እና ማቋቋም ነገረ-ስራ የትሕነግ ሠራዊት እንጂ ለአገራቸው በመንግስታቸው ትዕዛዝ አካላቸውን ያጡ ኢትዮጵያውያንን የማይመለከት ተደረገ፡፡ መሠሪው ትሕነግ ለረጅም እቅዱ አስልቶ ቀድሞ ከአማራ ነጥቆ ካካለላቸው አካባቢዎች መካከል ዳንሻ ዲቪዥን በተባለ ለም የእርሻ ስፍራ ላይ ሰላሳ ሺህ የሚጠጉ ወታደሮችን በማስፈር በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ መታ፡፡ ወታደሮቹን በኢኮኖሚ አቋቋመ፣ በወረራ ያካለለውን አካባቢ ስነሕዝብ ምጣኔ ለማዛባት ተጠቀመበት፡፡


ለአገሩ የደማውና የቆሰለው ሠራዊት ግን "ተሸናፊ" ተብሎ ከጎዳና ተዳዳሪነት እስከ ቀን ሰራተኛነት፤ ከአካል ጉዳት እስከ ስደት በኑሮው የተጎሳቆለ እንዲሆን አድርጓል፡፡ ይሕ ውትድርናን በማራከስ ሌላው ተወላጅ የማይጠጋው ለማድረግ የሠራበት ስልታዊ አካሔድ ነው፡፡

ስንቱን ባለጀብዱ ወታደር ስነልቦናው እንዲጎዳ፣ ስንቱን ባለትልቅ ማዕረግ ትንሽ ቦታ እንዲውል በማድረግ ወታደርነትን አራክሰው፡፡


Nico Belo የሚባል ሰው የቀድሞየኢትዮጵያመከላከያሠራዊት አባላት ከጦርነት በኋላ በገጠማቸው እጣ ፈንታ ላይ Problems of Ethiopian Ex-Combatants፡ በሚል በ2004 በሰራውዳሰሳ ከቀድሞ ሠራዊት አባላት ራሳቸውንያጠፉ፣ ለአእምሮ ሕመም የተዳረጉ ወታደሮች እንደነበሩ ፅፏል፡፡


"Three of the 37 interviewed Ethiopian exMengistu-soldiers told me about friends who had chosen to commit suicide, because they had not seen their families for years and did not dare to return to their distant homeland ‘empty-handed’.

They killed themselves, because they no longer had ‘any hope’. Those three ex-Mengistu-soldiers admitted that they themselves had considered suicide, but that they had rejected the idea because they felt responsible for their children at home."


ሠራዊቱን በትኖ የትም ወድቆ በማሳየት አዲሱን ትውልድ ከወታደርነት የመግፋት ዘዴን ተገበሩት፡፡ በጉርብትና ይሁን በዝምድና የሚያውቀው ወታደር የትም ወድቆ እያየው እንዴት ወታደር ይሆናል?

የቀድሞ ሠራዊትን የማራከስ ተግባሮች በትኖ ከማደኽየት በተጨማሪ በፍረጃ ማብጠልጠል መደበኛ ስራ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት አካል በነበረ ወታደር ላይ የተሸናፊነት እና ምርኮ ትርክትን በመንዛት የሞራል ስብራት ለመፍጠር ብዙ ተሠርቷል። ግንቦት 20 በመጣ ቁጥር አገራዊ ግዴታውን የተወጣን ሠራዊት ሬሳ በማሳየት "በተደምሳሽነት፣ በተሸናፊነትና በምርኮኛነት" ፈርጀው ቀጠቀጡት።


"የደርግ ወታደር" እየተባለ የስንቱ ቤተሰብ ቁስል ላይ ጨው ተደፋበት። በኑሮ ችግር ሜዳ በወደቀበት ግንቦትን ጠብቆ ደግሞ ተሸናፊነቱን ያውጅለታል፡፡ ድብቅ የትጥቅ ማስፈታት ስሌቶች ያልገባቸው ሁሉ የወያኔን አሸናፊነትና የደርግን ተሸናፊነት ያወሱ እየመሰላቸው በወገኖቻቸው ላይ የስነልቦና ጥቃት ተባበሩ፡፡

ሲያሰኛቸው "ከስርዓቱ እንጂ ከወታደሩ ፀብ የለንም" ሲሉ የሚሰሙት ትሕነጋውያን፣ "የድላችን ምንጭ የአላማችን ትክክለኛነት እንጂ የተለየ ጀግንነት አይደለም" እያሉም የሚመፃደቁት ትሕነጎች፣ ድል አድራጊነታቸውን ለመዘከር መድረክ ባገኙ ቁጥር ግን ውትድርና እና ጀግንነት የነሱ ብቸኛ መለያ አስመስለው ሌላውን ለማራከስ፣ ፈርጆ ለማግለልና ለማጥቃት ቦዝነው አያውቁም ነበር፡፡


ሌላው ይቅርና ሲሻቸው “የኢሕአዴግ ሠራዊት” እያሉ የጋራ ድል የሚሠጡትን ኢሕዴን/ብአዴን ሳይቀር መለስ ብለው "ሚናው ፖለቲካዊ እንጂ ወታደራዊ አልነበረም" ከማለት አልተመለሱም።

“ወታደራዊ ሚናው ትንሽ ነበር” ያሉትን የአማራ ጦር ግን "ለኢሕአዴግ ሠራዊት ቅነሳ" አላጡትም ነበር፡፡ ለታቀደው ትሕነጋዊ የወታደራዊ ጥቅለላ ፍላጎት ሲባል ከሠራዊቱ የወጣው የአማራ ሠራዊት ቀላል አይደለም፡፡

በደርግ ወታደርነት ሲረግሙት የኖሩት የኢትዮጵያ ጦር፣ ሜዳ የተወረወረው ከአማራ የወጣ ሠራዊት አባል እናሌላውም ኢትዮጵያዊ በ1983 ማግስት በደረሰበት ፍረጃ እና የኢኮኖሚ ድቀት ፤ ወታደርመሆን ክብር ሳይሆን ውድቀት መሆኑን ለሌላው በሚያስተምር መልኩ አራከሱት፡፡ አማራው "ደርግ" ተብለው ከተጣሉ የኢትዮጵያ ወታደሮች ሕይወት እንዲማር እና ውትድርናን እንዲጠላ የሰሩበት ደባ ነው።


እናም ውትድርናን ከአማራው ፍላጎትና ስነልቦና የመንጠቅ ስልታዊው አካላዊ እና ስነልቦናዊ ትጥቅ የማስፈታት ሒደት፣ ወታደርን ገፍቶ በድህነት ቅስሙን በመስበር፣ ወታደርን አራክሶ ከውትድርና በመግፋትና በማግለል፣ አግልሎም ለብቻ በመጠቅለል የተፈፀመ ነው፡፡

ሌሎች ተቋማዊ አግላይ ስሪቶችን እና የጥቅለላ አካሔዶችን በቀጣይ ዝግጅታችን እንመለከታለን፡፡ ዛሬ አማራ ላይ እየተፈፀመ ያለው ጦርነት ከትናንቱ የትሕነግ አዋጅ የቀጠለ፡ አማራን ከወታደራዊ አቅሞች የማፋታት እና እጅ የሠጠ ማህበረሰብ የመፍጠር ተልዕኮ ቅጥያ መሆኑን እያሰብን በቀጣዩ ዝግጅት እስከምንገናኝ ድል ለወገናችን እንመኛለን፡፡




 

Disclaimer: The opinions expressed in this article are those of the authors. They do not purport to reflect the opinions or views of the Amhara Popular Front ( APF) or its affiliates.














50 views0 comments

Comments


bottom of page