top of page
Writer's pictureከፋኖ ሽፈራው

የአማራ ወታደራዊ አቅሞች ምዝበራ (ክፍል -2 )

Updated: Sep 4, 2023


ከሽፈራው የሶማው


ዛሬ የጥህነግ የበኩር ልጅ በሆነው ኦነጋዊ ኃይል አማራ ላይ እየተፈፀመ ያለው ጦርነት ከትናንቱ የትሕነግ አዋጅ የቀጠለ፡ አማራን ከወታደራዊ አቅሞች የማፋታት እና እጅ የሠጠ ማህበረሰብ የመፍጠር ተልዕኮ ቅጥያ መሆኑን በቀዳሚ ክፍል አንስተናል፡፡


ትህነግ አማራን ከወታደራዊ አቅሞች ለመፋቅ በስነልቦና፣ በመሣሪያ ገፈፋ፣ በወታደራዊ ማራከስ ብዙ ማድረጉን አንስተናል፡፡ በዚህ ቀጣይ ክፍልም ትሕነግ የመራው አማራን ትጥቅ የማስፈታት ረጅም ሴራ እንመልከት፡፡


ሌላውን አግልሎ መጠቅለል፡


ትሕነጎች ሌላውን የማግለል ስራቸው ነባሩን የአገሪቱን ሠራዊት አመራርና አባል በሙሉ የደርግ ሠራዊት ብለው መጣላቸው እና ማራከሳቸው ብቻ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሳይሆን የኢሕአዴግ ሠራዊት መገንባት የቁጥጥር መንገዶች ነበሩ፡፡


ለፖለቲካ ፍጆታ ሲሉ ሲጠሯቸው ከነበሩት እና በወቅቱ "ነበሩ" ከሚሏቸው "21 የታጠቁድርጅቶች" አንድ ወታደር ሳያካትቱ፣ ለልዩነት ምክንያት የነበረው የኦነግ ሠራዊትም እንዲበተን በማድረግ፣ ለብሔራዊ መዋጮ እና አገራዊ ስዕል ብቻ "ከማረክናቸው በኋላ አብረውን የታገሉ" የሚላቸውን የኢሕዴን ሠራዊት አባላት ይዘው የአገሪቱንመከላከያበአንድ ወገንጦር እና አመራር ተቆጣጠሩት።

"ለውክልና እና መዋጮ" የአገሪቱ ሠራዊት አካል ሆነው እንዲቀጥሉ ተደረጉ የሚባሉት ደግሞ ጥያቄ ባነሱ እና ሚናቸውን ባወሩ ቁጥር “ምርኮኛ” እያሉ ትሕነጋውያን በምርኮኛነት በማሸማቀቅ የሚዘልፏቸው ናቸው፡፡


የትሕነግ ይሉኝታ የሌለው ወታደራዊ ጥቅለላ መገለጫ ማሳያው የኢትዮጵያ ሠራዊት ማለት "የኢሕአዴግ ሠራዊት" መሆኑ ነው።

ሕዝቡ የአገሪቱን ወታደራዊ ተቋማት "የአገር መከላከያ ሠራዊት" ሳይሆን "የኢህአዴግ ሠራዊት" ብሎ እስኪጠራቸው እና እስኪመለከታቸው የአንድ ፓርቲ እና አስተሳሰብ ስብስብ ተቋም እና ሠራዊት ተደረገ።


ወታደራዊ ተቋማት በትግሬ ብሔር ተወላጆች መያዝ ያስከተለውን ትችት ለመከላከል፤ ሲፈልጉ "ታዲያ ለመሞት ቢይዘው ምን ችግር አለው" ሲሉ፣ መለስ ብለው ደግሞ "ከእኛ የበዛው በብዛት ደርግን የታገልነው እኛ ስለሆንን ነው" ይላሉ። ብዙዎች ሳይመረምሩት የተቀበሉት ማደናገሪያ ነበር። የአገሪቱ ሠራዊት የት ደረሰ፤ የደርግን መንግስት ታጥቀው ሲዋጉ ነበር ያላችኋቸው ወታደሮች የት ደረሱ ያላቸው አልነበረም፡፡


የሚጠሉትንና የሚጠረጥሩትን ከኃይል ቁጥጥር እና ሚና ለማግለል ዘርፈ ብዙ የጥቃት መንገዶችን እየተጠቀሙ የወታደራዊ ኃይል ብቸኛ ቁጥጥርን ማስፋት የትሕነግ ወታደራዊ ሴራ ነበር፡፡ ወታደርን በማዋረድ ከወታደራዊ ተሳትፎ የማግለል እና ትጥቅ የማስፈታት ሌላኛው ግፍ ይህ ብቻ አልነበረም፡፡


ወታደራዊ ተቀዋማዊ አግላይነትን ማስፋት፤


ትሕነግ የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሚኒስቴር ተብሎ የተመሠረተውን መስሪያ ቤት በመሠረታዊ ተቋማዊ ይዘትና ቅርፁ ግን የትግራይ መከላከያ ሚኒስቴር አስመስሎ ፡ ወታደርነትን ከአገርነት ወደፓርቲ ጠበቃነት በቀየረ ተቋማዊ ፍልስፍና የገዢ ፓርቲው ተቋም በማድረግ ነበር አግላይነቱን ያሰፋው። የአንድ ብሔር ፍፁም ብልጫ ያለው ብቻ ሳይሆን የአንድ ፓርቲና ርዕዮተዓለም "የመጨረሻ ምሽግ" ተደረገ።


አንዳንድ ባለሙዎች እንደሚሉት ይሕ የአንድ ቡድን ወታደራዊ ጥቅለላ ለሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ግልፅ የስጋት ምንጭ የሆነ ነው፡፡ ምክንያቱም Dr. Kristen A. Harkness: የተባሉ ምሁር እንደሚሉት ወታደራዊ ተቋምን በአንድ ቡድን መሙላት ሌሎች ቡድኖችን ስጋት ውስጥ የሚጥል ነው፡፡

"Attempting to place a monopoly over the legitimate means of violence in the hands of a sole identity group inherently threatens excluded groups"

የዛሬውን ወታደራዊ ተግባር ለማወቅ የትናንቱን መረዳት በእጂጉ አስፈላጊ ነው፡፡

የትሕነግ የጥቅለላ አሠራር ከብሄር እና አመራር ሚዛን ብቻ ሳይሆን የመድሎ ወታደራዊ ፍልስፍናን በመትከልም የተፈፀመ ነበር፡፡


የስርዓቱ ወታደራዊ ፍልስፍና መመሪያ ነው ይባል የነበረውና "ቀዩ መፅሓፍ" ተብሎ የሚጠራው የ"አቢዮታዊ ዲሞክራሲ የአገር መከላከያ ሠራዊት" ማብራሪያ ሰነድ የአንድ ብሔር ቀጣይ ወታደራዊ ቁጥጥርን ከሚያስረግጡ አግላይ አስተሳሰባዊ የአሠራር መገለጫዎች አንዱ ነው፡፡


በተጨማሪ የአንድ ፓርቲና ርዕዮተ ኣለም አገልጋይነቱን፤ "መከላከያ ሠራዊቱ የአቢዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓቱ የመጨረሻ ምሽግ ነው" ሲል አስቀምጦት ነበር፡፡

ይሔ በፖለቲካ አመለካከት ከኢሕአዴግ ልዩነት ላለው፣ በአቢዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ለማያምንአማራም ሆነ ሌላው ሕዝብ የአገሪቱን መከላከያ ሠራዊት ተቋማዊ ባዕድነትና መገለል በከፍተኛ ደረጃ የጨመረው ነበር።


በአቢዮታዊ ዲሞክራሲ ወታደራዊ ተልእኮ መሠረት ምሽግነቱን እና ርዕዮቱን መጠበቅ፡ ማመን፣ ግዴታም ፡ መገምገሚያም፡ የሙያ እና ማዕረግ እድገት መስፈሪያም በተደረገበት የሌላ ርዕዮተ-ዓለም ፖለቲካዊ እምነት ይዞ የወታደሩ አባል መሆን ውግዘት ሆነ፡፡


ከአገር በታች ሁሉንም አመለካከቶች እና አደረጃጀቶች በእኩል መመልከት ያለበት ተቋም የገዢው ፓርቲ የፖለቲካ አመለካከት እና አቋም ነጸብራቅ ሆኖ አግላይነቱን አሰፋው፡፡

የአቢዮታዊ ዲሞክራሲ ወታደራዊ አስተምህሮ እንደፖለቲካው ሁሉ በአሠራር እና መመሪያ አማራውን የሚያገል፤ ሌሎች ብሔሮችን ኋላ የሚያሰልፍ፣ የተቋሙን አመራርነት በዚያው አንድ ቡድን ቁጥጥርን የሚያስቀጥል ተቋማዊ አሠራር እና ፍልስፍና የተከለ ነበር ።


የአቢዮታዊ ዲሞክራሲ የፍረጃ ባሕል በዚሁ ተቋም ውስጥ ቀጥሎ፣ ወታደር፡ በተልዕኮው ሳይሆን በፖለቲካዊ አመለካከቱና ዝንባሌው የሚከሰስበት እና የሚፈረጅበት ተቋም ሆነ፡፡

ከአማራው ወገን ጥያቄ የሚያነሳ ወታደር ሁሉ በደርግነት ፣ ነፍጠኝነት ፣ ቅንጅትነት ፣ ግንቦት-7፣ እየተባለ በሰበብ አስባቡ ሲባረር የኖረበት ነው ። ዛሬም መልኳን ቀይራ እየመጣች ስለመሆኑ እያሰብን እንቀጥል፡፡

በአስርሺህዎች የሚቆጠሩ የአማራ ወታደራዊ መኮንኖች በየሰበቡ እንዲባረሩና ከፍተኛ ወታደራዊ ማዕረጎችና አመራርነት በአንድ ወገን ቁጥጥርና ይዞታ እንዲቀጥሉ ለማድረግ ተጠቅመውበታል።

አማራ በየጊዜው በተነቀሉ ወታደራዊ መኮንኖችና አመራሮች የተነሳ በተቋሙ ውስጥ የኔ የሚላቸው ጀግኖችና ምልክቶች እንዳይኖሩት አደረገ። እናም የራሱ ተቋም እንዳይመስለው አደረገ።

የአማራ ወታደራዊ ተሳትፎ ከመካከለኛ በታች ባለው ወታደራዊ መዋቅር ውስጥ ነበር፡፡

ወደ ከፍተኛ አመራርነትና አዛዥነት ሊደርሱ የሚችሉ መኮንኖች በፍረጃ ፖለቲካዊ ባህሉ እየተጠበሱ እንዲለቁና ጡረታ እየተባለ እንዲባረሩ ሆኗል፡፡

በፀረ-ደርግ ትግል የኢሕዴን ጦር ውስጥ የነበሩትን አማራዎች እንኳ መርጦ ያስቀረበትና ያባረረበት መለኪያ በወሎ እና ዋግኸምራ አካባቢ የነበሩትን ከኃይማኖት እና ብሔረሰብ ምንጭ መለኪያነት በሚነሳ መስፈርት፣ አማራን ከወታደራዊ ሚናዎች የመንቀል ሴራ አካል ነው።


ብዙዎች ለከፍተኛ ወታደራዊ ማዕረግ ሊበቁ ይችሉ የነበሩ አማራዎች አስቀድሞ በሚሠራ ሴራ ከተቋሙ ተጠርገው እንዲለቁ ተሠርቷል። ዛሬ የትንቱን ለመድገም የተነሱት የኦሮሞወታደራዊመኮንኖችምበኦነግነትተፈርጀውየሚሸማቀቁአልፎም የሚባረሩ ነበሩ። ሆን ተብሎ በሚሠራ ሴራ የተገደሉትንና የተሠወሩትን ቤቱ ይቁጠራቸው። ወታደራዊ አግላይነትና ቁጥጥር ግን በተለያዩ ግን ተመጋጋቢ በሆኑ ስልቶች፣ ስፋታቸው እና ተፅእኗቸው እያደገ በሚሔድ አግላይ የጥቃት ስልቶች የተሠራ ነው፡፡


ወታደራዊ እና ተቋማዊ አግላይነቱ በአገሪቱ ወታደራዊ መዝገበ ቃላት ጭምር የሚገለፅ ነበር፡፡

የመከላከያ ሠራዊቱ ወታደራዊ ቋንቋ መዝገበ ቃላት የተቋሙን አግላይነት ስፋት አመላካች ያደረገው የተቋሙ አመራር፣ አስተሳሰብና ዓላማ ብቻ ሳይሆን የትሕነግታጣቂዎች የደርግን ስርዓት ለመጣል የተዋጉበትንወታደራዊስያሜ እና የወታደራዊ ፍችዎች መዝገበቃላት በትግርኛ ቋንቋ ቀይረው የአገሪቱ ሠራዊት ቋንቋ አደረጉት። የወታደራዊ አደረጃጀቶች ፣የስራ ክፍሎች፣ ስምሪቶች ወዘተ መጠሪያዎች ከአንድ ወገን ንግግር ተስማሙ። የተቋሙ ባዕድነት ያሰፋው እንዲህ ነው፡፡


ትግርኛ ተናጋሪዎች ጠቅልለውት በነበረው መከላከያ ሚኒስቴር የስራ ቋንቋ ብዥታ መኖሩ ብዙም የሚደንቅ አልነበረም፡፡ የሚደንቀው “የቋንቋ ጭቆና ደርሶብኛል ሌሎቻችሁም ደርሶባችኋል” ብሎ የሰበከው ትሕነግ የራሱን ቋንቋ በፖለቲካና ወታደራዊ ተቋማት መጫኑ ነው፡፡ የሚቆጨው፡ እንዲህ ያለው ተቋም ውስጥ የነበሩ አማራዎች በጠቅላይነትና ትምክህት እየተፈረጁ ሲወነጀሉና ሲቆስሉ መኖራቸው ነው፡፡ ይሔ ዛሬም ያልተለወጠ ወታደራዊ መግባቢያ ቋንቋ የተፅእኖው ስፋት ማሳያ ነው።

ሆኖም የኢሕአዴግ ጦር ፡ ለአግላይ አገራዊ መገለጫዎች የሚገዛ የፓርቲ ሠራዊት በመሆኑ የትሕነግን ፖለቲካዊ ብያኔዎች ወርሶ የቀጠለ መሆኑ አግላይነቱን ያሰፋለት ነበር፡፡


የአንድ ወታደር ሙያዊና አገራዊ ቃልኪዳን ከሰንደቅ አላማው የተሳሰረ ነው። የሚሞትለት ፣የሚደማለት፣ መለዮ የለበሰለት እና ሕይወቱን አስይዞ የሚጠብቀው የሙያዊ ክብሩ መገለጫ ነው። አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ደግሞ የኢትዮጵያውያን የፀረ-ቅኝግዛት እና አርበኝነት ምልክት፣ የአፍሪካውያን የነፃነት መለዮ ነው፡፡ ዛሬ ከአገራዊ የልዩነት ምልክቶች አንዱ የሆነው የኢፌድሪ ሠንደቅ ዓላማ ግን የትናንት ገዢዎች ሕግ እንጂ ፍላጎት ያፀናው ነው ለማለት አያስደፈርም፡፡


ይሕን የተረዳው ትሕነግ፣ በሁለት አገረ-መንግስት እሳቤ ሲጓዝ የኖረው ትሕነግ፣ "ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት የለም፣የጨቋኞች ማንነት ነው" የሚለው ትሕነግ ደግሞ የጥቅሙ መሠረት እንዲሆነው የተከለው የመድሎ ስርዓቱ እንጂ የአገር ፍቅርና ታማኝነት እርሙ ነውና በራሱ አምሳል እና ርዕዮት ቀረፃቸው፡፡

የትሕነግ ሠንደቅአላማ እና ሕገመንግስት ደግሞ ከሰፊው አማራ አይገጥምም። ይሔም የተቋሙን ገፊነት እና የአንድ ወገን ተቋምነት በከፍተኛ ደረጃ አሳደገው። የነዚህ ድምር ውጤት የአማራን ልጆች ከወታደራዊ ተቋሙ አባልነት እና ተሳትፎ በመግፋት፣ አማራን በወታደራዊ አቅሞች ለማዳከም ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡


የጨነቀለት ፡ የቀድሞ ወታደር እና የቀድሞ ባንዲራን ፍለጋ፤


የኢትዮጵያ ፖለቲካ-ኢኮኖሚ ፍፁም ቁጥጥርን ከመያዝ አኳያ የኤርትራን መገንጠል ከማንም በላይ የሰበከው ትሕነግ፣ ከማንም ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ኃይል በላይ የሚያውቀውና አብሮት ደርግን ከጣለው የኤርትራ ኃይል ጋር በ70ዎቹ መጀመሪያ መክረውበት በይደር ያሳለፉት የባድመ ድንበር ጉዳይ በደርግ ውድቀት ማግስት ጦርነት ሆኖ ብቅ አለ፡፡


ይሔኔ በምርኮኛነት ፣ በተሸናፊነት ፣ በተደምሳሽነት እየተገለፀ፣ "የደርግ ወታደር" ተብሎ የትም የተጣለው የኢትዮጵያ ወታደር፡ "የቀድሞ ጦር" የሚል የመጠሪያ ለውጥ አገኘ፡፡ በ"ተሸናፊነት" ተፈርጆ የተካደው ጀግንነቱ፣ በፀረ-ሕዝብነት ፍረጃ የተሸፈነው የአገር ፍቅሩ፣ በ"መብት ረጋጭነት" የተኮነነው የአገር አንድነት ምኞቱ፣ በ"ደርግነት" ብያኔ ለማሳነስ የተሳለው ኢትዮጵያዊነቱ ተፈለገ፡፡ የጨነቀለት!

ያን ጊዜ ነበር ከደርግ ጋር ተቀበረ የተባለው የኢትዮጵያ አርበኞች የጀግንነት ሽለላ፣ ፉከራና ቀረርቶ ከፍ ብሎ እንዲሰማ የተከፈተው፡፡ የጨቋኞች ምልክት ተብሎ በጨርቅነት የተወገዘው ሰንደቅ ኣላማ ከተሸሸገበት ወጣ፡፡ "የብሔረሰቦች እስር ቤት" ተብላ የነበረችው ኢትዮጵያ በእናት ክብር መገለፅ ጀመረች፡፡


የቀድሞ ጦር እና የቀድሞ አርበኝነትን ፍለጋ ጦፈ! የጨነቀለት!

የቀድሞ ጦር እንዲዘምት ምን ይደረግ ሲባል የቀድሞ ሰንደቅ እና የአርበኝነት ዝማሬውን ማንሳት ፍቱን ነው ተባለ፡፡ እንደጠበቁት ደሙን ገብሮ አገር አስረከበ፡፡ የተፈረጀው ድል አድራጊነት በተቃራኒው ተመሰከረ፡፡

የዚያ ጦርነት ፍፃሜም ለአገር ክብር የተዋደቁትን ልክ እንደ ደርግ ዘመን የኢትዮጵያ ወታደሮች በመክዳት የተጠናቀቀ ነበር፡፡


Nico Belo ከባድመ ጦርነት በኋላ ያገኛቸው ከሁለት የሚሆኑ ዘማቾች በአገሪቱ ባለስልጣናት መከዳታቸውን ፤ ትምህርታቸውን አቋርጠው እንዲዘምቱ ቃል የተገባላቸው ስራ፣ ቤትና መሬት መቅረቱን በቁጭት እንዳነሱለት ይጠቅሳል፡፡

"Nearly all of the combatants demobilised after the war with Eritrea in 2000 told me that they had a bitter feeling of being neglected by the Ethiopian authorities and the Ethiopian public. They said they had been promised jobs, houses and land if they joined the army. They had therefore stopped their education and joined the forces"


ሆኖም ከዘመቱ ብዙ ቃል የተገባላቸው ወጣቶች በ4ሺህ ብር ከመሸኘት አልዳኑም፡፡ ተቋሙን እና መከላከያን እንዲጠሉት ለሌላውም በደል እንዲያስተጋቡ በማድረግ ለማግለል እና መድሎ አስተዋፅኦ ያደረገ ሒደት ነበር፡፡

ያ የአገር አድን ጥሪ የተደረገበትና አገር የታደገው ድባብ ታዲያ በትህነግ አመራር ተወግዟል፡፡ በአማራ ላይ የተጀመረውን "ትጥቅ የማስፈታት ፕሮጀክት" የሚቀለብስ፣ የአገር ፍቅር፣ የአርበኝነትና ጀግንነት ስነልቦናውን መልሶ የሚያነሳሳ ነበርና መለስ ዜናዊ ከኤርትራ ጋር መዋጋቱ ብቻ ሳይሆን የአማራ እሴት የሚሏቸው የቀድሞ ወታደርና የቀድሞ ሰንደቅ ፣ በፉከራና ሽለላ ታጅበው ባድመ መዝለቃቸውን በፀፀት ተቸው፡፡ "አንጃ" ያላቸው ትግሬ ጓደኖቹን ለጦርነቱ ተጠያቂ ባደረገበት ፅሁፍ "ፉከራና ቀረርቶ" ከመቃብር ተነስተው ወጡ እያለ ያን ሁነት ረግሟል፡፡


ስንቱ ካለቀበት የባድመ ጦርነት በኋላ የመጣው መከላከያ ሠራዊት፣ የሚበዛውን ዘማችና የቀድሞ ጦር በአነስተኛ ጉርሻ ሸኝቶ ብልጫንና ቁጥጥርን ለማስከበር የተሠራ ነው፡፡ ደርግን ለመጣን ተዋግቶ ወደ ልማት የተሸኘው የትሕነግ ሠራዊትም ከቀድሞው ጦር ጋር በጦርነቱ ሰበብ ወደ መከላከያ በመመለሱ የቁጥጥ ሚዛን አስጠባቂ ሆነ፡፡


ማግለልና ቁጥጥሩ ግን በአዲስ ገፅታ ቀጠለ፡፡ የቀድሞ ጦር እና የኢሕአዴግ ጦር በሚል ተቋሙ የፍረጃ ባህሉን ቀጠለ፡፡ ግንቦት 20 በመጣ ቁጥር የባድመ፣ ቡሬና ፆረና ጀግኖች ሁሉ የደርግን "ድምሰሳ" የማክበር ግዴታ ተጣለባቸው፡፡ የቀደመ ሠራዊታቸው እንዴት እንደተጠቃ የባለጊዜዎቹን ትረካ መስማት ግዴታቸው ነበር፡፡ የባድመ ጀግኖችን የደርግ ተሸናፊ አድርገው ይነግሯቸዋል፡፡


የመድሎና ጥቅለላ ቀዩ መፅሓፍም የተዘጋጀው ከኤርትራ ጦርነቱ በኋላ ነው፡፡ የመከላከያ ሠራዊት ሪፎርም ሲሰበክ ሰንደቁም፣ቀረርቶና ፉከራውም፣ የእናትአገር ዝማሬም "ከትግሬ አንጃዎች" ጋር ተሸኙና ወታደራዊ ንግግሮች ሁሉ የፖለቲካው ግልባጭ ሆነው በአቢዮታዊ ሠራዊት፣በልማታዊ ሠራዊትነት ተለወጡ፡፡ ከእነዚህ የማይጣጣም ወታደርነት አይሆነውም፡፡


አማራው ከወታደራዊና የኃይል ሚዛን ተገዳዳሪነት እንዲወጣ ሁሉም አማራጭ በስነልቦና ፣ በወታደራዊ ተሳትፎ ገደብ እንዲሁም በወታደራዊ ተቋማዊ በደልና ማግለል የደረሰበት መሆኑ ከሞላ ጎደል የአገር መከላከያ ሠራዊት አባልነትን እንዳይቀበለው የሚያደርግ ውጤት ማሳየትና ራሱን ከውትድርና የሚያገል ማህበረሰብ የመሆን ምልክቶች አምጥቷል፡፡


ለዚህ ደግሞ የተለያዩ፣ ተመጋጋቢ የማግለልና መግፋት ስልቶች በአንድ ጊዜና ሳይቆራረጥ መሠራቱ ትልቅ ጫና አምጥቷል፡፡ በደርግ ዘመንም፣ ከኢህዴንም፣ ከኤርትራ ጦርነት በኋላም በትሕነግ ፈራጅና አግላይ አመራር ተገፍቶ በምሬት የተበተነው ሠራዊት የወታደርነት ሙያን ቢያደንቅም በትህነግ ደባ የተሞላውን የመከላከያ አባልነትን እንዲሸሽ እና የመከላከያ ተቋምን እንዲጠራጠር የሚያደርግ ነበር፡፡


ይሔ ሁሉ ሒደት ኦነግ መራሹ ፀረ-አማራ ኃይል ዛሬ በሚያከናውነው ጦርነት እና በአገር መከላከያ ውስጥ ለሚፈፅማቸውና ሊፈፅማቸው ለሚወዳቸው ተግባሮቹ ማነፃፀሪያዎቻችን ብቻ ሳይሆኑ ለአማራ ወገናችን ንቃት መሠረት የሚሆኑ ናቸው፡፡ ስለሆነም ረጅሙና ውስብስቡ አማራን ከወታደራዊ አቅሞች የመለያየት ነባር ሴራዎች ማቅረባችንን እንቀጥላልን፡፡ በቀጣይ ዝግጅታችንም በአማራ ገዳይነት የተሳለው መከላከያ ታሪኮች እናቀርባለን፡፡ ድል ለአማራ!



 

Disclaimer: The opinions expressed in this article are those of the authors. They do not purport to reflect the opinions or views of the Amhara Popular Front ( APF) or its affiliates.




20 views0 comments

Comments


bottom of page