top of page
Writer's pictureAmhara Fano People's Force (AFPF)

የኢትዮጵያ የመከላከያ ሚንስትር ተብዬው የጦር ነጋሪት ጉሰማ

Updated: Aug 29, 2023

የፋሽስታዊው መንግሥት የመከላከያ ሚንስትር ዶ/ር አብርሃም በላይ ከአሸንድዬ፣ ሻደይና ሶለል በዓል ጋር አያይዞ በተረጋገጠ የማኅበራዊ ሜዲያ ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሑፍ የአማራ ታሪካዊ እርስት የሆኑት ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያን የሃገሪቱን መከላከያ በመጠቀም ከባለርስቱ በጉልበት ተነጥቀው ለሕወሃት እንደሚሰጡ በድፍረት ከማወጁም በላይ ጉዳዩን በተመለከተ በፋሽስቱ አብይ አህመድ ውሳኔ መተላለፉንና የዚህን ውሳኔ አፈጻጸም ለማስተጓጐል በሚነሳ ሃይል ላይ የአገዛዙን ሰራዊት በመጠቀም እርምጃ እንደሚወሰድ ዛቻውን አስተላልፎአል።


የአማራ ሕዝባዊ ግንባር ለሠላሳ ዓመታት በሕወሃት ወረራ ተይዘው የነበሩት የአማራ እርስቶች የአማራ ሕዝብ በከፈለው መስዋእትነትና ባስመዘገበው ድል ዛሬ በባለእርስቱ አማራ እጅ ባስተማማኝ ሁኔታ እንደሚገኙ የሚረዳም ቢሆን በመንግሥትነት ስም የሀገሪቱን ከፍተኛ ሥልጣን የያዘ ግለሰብ ለአማራ ህዝብ ከፍተኛ ንቀትን በማሳየት ያሰማው ድንፋታ አገዛዙ የአማራን ህዝብ ተፈጥሮአዊ የህልውና መብትና ጥቅሞች በማናቸውም መንገድ ለመጉዳት የሚያደርገውን አካሄድ ሊደብቀው ከማይችልበት ደረጃ መድረሱን ያጋለጠ ሆኖ አግኝቶታል። ይህ በፋሽስታዊው መንግሥት የመከላከያ ሚንስትር በኩል የተስተላለፈው ዋይታ መሳይ ዛቻ አዲስ ያይደለ በመሆኑና እርሱ ከሚያገለግለው ደም አፋሳሽና አገር አፍራሽ የኦነግና ትህነግ ጥምር ሥርዓት የተለየና የተሻለ ፍትሐዊ አሠራር የማይጠበቅ በመሆኑ የመልእክቱ ዋና ዓላማ አጀንዳ ማስቀየር እንደሆነ ግልጽ ነው። ዋና ዓላማው የአማራን ህዝብ የትኩረት አቅጣጫ ለመበተንና በየ አውደ ግንባሩ እየደረሰበት ላለው ሽንፈት አቅጣጫን ማስቀየሪያ አጀንዳ ለመወርወር እንደሆነ እንረዳለን።


የዶ/ር አብርሃም የወረራ ዛቻ ሥራ ላይ ዋለም አልዋለም፣ አማራው እርስቱን ዳግመኛ ላለማስነጠቅ ከፍተኛ ዝግጅት በማድረግ ማንኛውምን ዓይነት ጥቃት በመጠባበቅ ላይ ነው። ወቅቱ የአማራ ህዝብ እርስቱን ዳግመኛ ላለማስነጠቅ ማንኛውንም ዓይነት ወረራ ለመመከት በአስተማማኝ ቁመና ላይ የሚገኝበትና በተጠንቀቅ የሚጠብቅበት መሆኑን አጥቶት እንዳልሆነ ይታወቃል። በመሆኑም ዛቻው የአብይ አህመድ ወራሪ ኃይል በአማራ ክልል በፋኖ እየደረሰበት የሚገኘውን የዕለት ተዕለት ሽንፈት ለማድበስበስና የመተንፈሻና እንደ አዲስ የመደራጃ ጊዜን ለማግኘት የተወረወረ አጀንዳ ሊሆን እንደሚችልም መገመት ይቻላል። በአማራው ልጅ ፋኖ ተዳክሞ የትፍረከረከው የአብይ አህመድ ጦር ሌላ ወረራ ሊያካሂድ ይቅርና በአንዳንድ ከተሞች ውስጥ በመሰጠም ዙሪያውን የከበበው የፋኖ እስረኛ ከሆነበት ሰብሮ የመውጣትም አቅም እንኳ የለውም።


የአቢይ አህመድ የኦነጋውያን ሠራዊት ሰላማዊ ዜጎችን፣ እናቶችን፣ ሕጻናትን እና አዛውንት አሮጊቶችን በከተማ መኻል ከቤት ቤት አሰሳ እያደረገ ከማረድ በቀር ወደ ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያ ዘልቆ በጉልበት የአማራን እርስት ለሕወሃት የማስረከብ ዐቅም እንደሌለው ለመረዳት በፋኖ የተደመሰሱበትን ትቶ የተማረኩበትን ብቻ መመልከት በቂ ነው። ፋሽስቱ አቢይ አህመድ ማናቸውንም የከባድ መሣሪያ፣ የድሮንና የዘመናዊ ቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን ቢጠቀም ህልውናውን ለማስጠበቅ ቆርጦ የተነሳው የአማራ ሕዝብ የያዘውን የህልውና ትግል ግቡን እስኪመታ ላይጨርሰው አልጀመረውም።


ከላይ የተገለፀው አሁናዊ ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ የሚከተሉት ሁለት ነጥቦች ግልጽ ሊሆኑ ይገባል፥


  1. የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞንና የራያ ጉዳይ በዋናነት የእርስት ባለቤትነት ጉዳይ ቢሆንም የማንነትንም ጥያቄ ያካተተ ነው። በመሆኑም የጥያቄው ባለቤቶች አማራዊ ማንነታቸውን በኃይል የተነጠቁት የአካባቢው ነባር ነዋሪዎችና መላው አማራ እንጅ ብአዴን ባለመሆኑ በጉዳዩ ላይ ብአዴን የመወሰን ህጋዊም ሆነ ሞራላዊ መብት የለውም።

  2. የአማራ ዐፅመ እርስቶች ጉዳይ እርስትን በማስመለስ ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን በአካባቢዎቹ ይኖሩ በነበሩ አማሮች ላይ ለደረሰው ጭፍጨፋ ፍትሕ የምንፈልግበት የአማራ ትግል አስኳል መሆኑ ለወዳጅም ለጠላትም ግልጽ ሊሆን ያስፈልጋል።


የአቢይ አህመድ ሠራዊት ለዚህ ለተባለው ወረራ በአጋሩ የሕወሃት ሠራዊት እንደሚደገፍ የታወቀ ቢሆንም አማራው በከባድ መስዋእትነት ከእጁ የገባውን እርስቱን አሳልፎ እንደማይሰጥ የሚያከራክር አይደለም። በተለይ በወልቃይት ሕወሃት የአማራን እርስት ሲነጥቅ የዛሬ 33 ዓመት በጅምላ የጨፈጨፋቸው የወልቃይት አማሮች ደም ዛሬም ፍትሕ እያለ እየተጣራ ነው። ከስደት ተመልሰው በአባቶቻቸው እርስት ላይ እንደገና የተሠየሙት የወልቃይት፣ የጠገዴ፣ የጠልምትና የራያ አናብስት ደም ጎርሰው ደም ለብሰው የአቢይንና የሕወሃትን ወራሪ ኃይሎች መቼ በመጡ እያሉና በር በር እያዩ እየጠበቋቸው ይገኛሉ። የአማራ ሕዝብ የህልውና ትግሉን ላይጨርስ አልጀመረውም።


የአማራ ሕዝብ ያሸንፋል፦

መነሻችን የአማራ ህልውና

መዳረሻችን የኢትዮጵያ አንድነት፦



45 views0 comments

Comments


bottom of page