top of page

የኦሮሞ ልሒቅ የኢኮኖሚ ዘር ማጥፋት (ክፍል-1)

Updated: Sep 4, 2023

የኦሮሞ ልሒቃን በአማራው እና በአገር ደረጃ እየፈፀማቸው ያሉ ፍጅቶች እና ውድመቶች፡ መልከ-ብዙ መሆናቸውን በመላ አገሪቱ ፡ በተለይ ደግሞ በአማራው ላይ እየተስተዋሉ ያሉ ዓይነተ-ብዙ ሰብዓዊ ስቃዮች እና ፍጅቶች ምስክር ናቸው።

ልሒቁ ከጥፋት አምዶቹ መካከል፡ ከዚህ ቀደም የባሕል ዘር ማጥፋት ትርክቶቻቸውን እና ተጨባጭ ድርጊቶቻቸውን በዚህ ራዲዮ ዝግጅታችን አቅርበናል።

ዛሬ ይሔው የኦሮሞ ልሒቅ ፤ በሙያተኞች አጠራር፡ "የኢኮኖሚ ዘር ማጥፋት (economic Genocide)" የሚሉትን ፣ አማራውን በኢኮኖሚ ለማጥፋት እና ለማውደም የሚሠሩትን ሴራ እንመለከታለን።

-- መሸጋገሪያ -

[የኦሮሞ ልሒቅ የኢኮኖሚ ዘር ማጥፋት (economic Genocide) እንዴት እየሆነ ነው!?]



በጭንቅ ሰሞን ለእርማት እና ምክር ብቅ እያለ አስተያየት የሚሰጠው የኦሮሞ ብሔርተኝነትንም ፋሽዝምንም ያዋለደው ሌንጮ ለታ በቅርቡ አንድ ነገር ተናገረ።

በድሕረ-1983 የፌደራል ስርዓቱ ሲካለል፡ "ኦሮሚያ" ተብሎግዛቱ ሲካለል እና ስፋቱን ሲያውቁ ኦሮሞዎች ራሳቸው ደንግጠዋል" አለ። ከኢትዮጵያ ላይ ይሔንን ያሕል መሬት የእናንተ ነው መባሉ የድንጋጤው ምንጭ ነው። ይሔ ንግግር ዞሮ የዘር ማጥፋት መነሻ የሆኑ አስተሳሰቦችን የወለደ አከላለል ነው። አንድም ኦሮሞ ያልሆኑ ሕዝቦችን በኦሮሞ ስር በማጠቃለል "የግዴታ መዋጥን- Forced assimilation አስከትሏል ፤ ሁለትም "ድንጋጤ የፈጠረው" ብዙ ሀብት የሚገኝበት ሰፊ ግዛት በኦሮሚያ ስር መካለል፥ "የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያለእኛ ሕልውና የለውም"፣ "ኢኮኖሚያችን በሌሎች ብሔሮች ተይዟል" ከሚሉ አስተሳሰቦች የሚመነጩ ትርክቶች ተክሏል።


ይህ የልሒቃኑ የዘር ማጥፋት አስተሳሰብ ኢኮኖሚያዊ አንድምታ ልዩ ልዩ ትርክቶችን የሚከተል ሆኖ የቀጠለ ነው። የኦነጉ ዳውድ ኢብሳ "ኢትዮጵያ ለኦሮሚያ ግብር ትክፈል" ሲል የብዙዎቹን አመለካከት ወካይ አነጋገር እና ስሜት የገለጠ ነው። የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራር በቀለ ገርባ፥ " ሱቅ ሔዳችሁ በኦሮምኛ ካላነጋገሯችሁ ከእነሱ አትግዙ" ሲል አስተሳሰቡ በአንድ ፓርቲ የታጠረ ሳይሆን የልሒቃኑ የጋራ አስተሳሰብ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።ይሕ "ከሐበሸ ቤት ማንኛውንም ነገር አትግዙ" የሚል ቅስቀሳ የኢኮኖሚ ዘር ማጥፋት (economic genocide) መገለጫ ነው።

ሩዋንዳ በዚህ መሠሉ ትርክት አልፋለች።


የኦሮሞ ልሒቃን በሌሎች ላይ በተለይ ደግሞ በአማራው ላይ የኢኮኖሚ ጄኖሳይድ የመፈፀም አላማቸውን ከነባር ትርክቶቻቸውም በተጨማሪ ስልጣን ላይ ያሉት ልሒቃን በተለያየ ወቅት ያንፀባረቋቸውን አቋሞችና አመለካከቶች በደንብ መመርመር እና መረዳት ጠቃሚ ነው።


ሁልግዜም የልሒቁን ፋሽስታዊ አላማዎች በመግለጥ ሰፊውን ኢትዮጵያዊ የሚያነቃው ሽመልስ አብዲሳ፡ የቡድናቸውን አጥፍቶ የመዳን አላማ የገለፀበትን ንግግር ለወገኖቹ አሰምቷል።

እንጥቀሰው፤

"አሁን እኛ ኦሮሚያ ከልክ በላይ እየለማች ነው፣ ሌላው ክልል ከልክ በላይ እየተጎዳ ነው። ይህ ደግሞ እየሆነ ያለው የፌዴራሉን መንግሥት ኦሮሞ ስለተቆጣጠረው ነው።"


ይሔ አባባል ሕሊና እና አእምሮ ላለው ኢትዮጵያዊ ምን ስሜት ይሰጣል?

ኦሮሚያ ከልክ በላይ ስትለማ፣ ሌላው ክልል ከልክ በላይ ሲጎዳ ከመመኘት በላይ ምን ያለ የዘር ማጥፋት አስተሳሰብ ይገኛል!?


የሰዎቹን ዘር አጥፊ አመለካከት የሚገልጠው እና እጅግ አሳዛኝም የሚያደርገው ፥ "ኦሮሚያ ከልክ በላይ እየለማች ሌላው ክልል ከልክ በላይ እየተጎዳ ያለው የፌደራል መንግስቱን ኦሮሞ ስለተቆጣጠረው" እንደሆነ በታላቅ ስኬትነት ተናግሮታል።

የፌደራል መንግስት ስልጣን የሚያዘው ፡ የራስን ክልል ከልክ በላይ እያለማህ ሌላውን ክልል ከልክ በላይ ለመጉዳት አድርጎ ከመረዳት በላይ ዘር አጥፊነት ከዚህ በላይ አገር አፍራሽነት ከየት ይመጣል!?

ይሔ አመለካከት ስልጣን የተቆጣጠረውም ሆነ ስልጣን ያልያዘው የኦሮሞ ልሒቅ እምነት እና ተግባር ነው።

በኢትዮጵያ እየተፈፀመ ያለው አብዛኛው ነገር ከዚህ አመለካከት እና እምነት የሚመነዘር ነው !!


በእርግጥ ለአማራ ልሒቅ እና ሰፊው ኢትዮጵያዊ መስማት የሚፈልጓቸውን "ደግ ወሬዎች" በማውራት ያደነዘዘው አብይ አሕመድም ፣ በተለያየ ወቅት ይሔንን የኢኮኖሚ ጄኖሳይድ ጠቋሚ አላማዎች ተናግሯል።

አብይ አሕመድ ፡ በአንድ ወቅት የኦሮሞ ልሒቃንን በመሰብሰብ ፣ "ለኦሮሞ ካልሠራሁ ለማንም ልሠራ አልችልም። አማራዎችን ከፋፍያቸዋለሁ፣ እናቴ አማራ ነች ብዬ አሳምኛቸዋለሁ" በማለት የቆመላቸው እና የሚሠራላቸው ለእነሱ ስለመሆኑ አረጋግጦላቸዋል። እነሱም በምላሹ ከኦሮሚያ እሱ ላይ ተቃውሞ እንዳይነሳ እንዲሠሩ አሳምኗቸዋልና፡ ይሔው ዛሬ ፤ 'አብይ የወደደውን ደግፈው፥ የጠላውን ተቃውመው' የሚሰለፉ አካላትን ፈጥሯል።


የኦሮሞ ልሒቃን፡ የጥቃት ማዕከላቸው አማራ ስለመሆኑ ፡ ራሳቸው በተለያየ ወቅት የተናገሯቸው እና ኋላ ላይ የፈፀሟቸው ተግባራት ምስክር ናቸው።

አብይ አሕመድ ፡ በአንድ መድረክ የተናገረው ንግግር መለስ ዜናዊ በሆነ ዘመን ከተናገረው ጋር ብቻ ሳይሆን ከፈፀመው በደል ጋር የሚገጣጠም ነው።

መለስ፥ በአንድ ወቅት የትግሬ ነጋዴዎችን ሰብስቦ ፥ ...." እናንተ ጠርሙስ እና ጭን ውስጥ ተደብቃችሁ፡ የጎጃም ባላገር መጥቶ የአገሪቱን ወጪና ገቢ ንግድ ተቆጣጠረው" ማለቱ ይወሳል። አብይ አሕመድ ደግሞ በአንድ መድረክ ላይ ፥ "በአንድ መንደር ባለሀብት የተያዘ ኢኮኖሚ ይዘን ስለአገር ኢኮኖሚ አላወራም" ማለቱ ተሰምቷል።


በእነዚህ ሰዎች አስተሳሰብ ፡ የቱንም ያሕል በላብህ ሠርተህ ብትለወጥ፣ ከሆነ አካባቢ በርከት ካልክ ስሕተት ያደርጉታል። በተመሳሳይ፡ ሌላኛው የኦሮሞ ልሒቅ እና በድሕረ-ኢሕአዴግ : 'ከደሙ ንፁሕ ተደርጎ' የአብይ አሕመድ ባለሟል የሆነው ግርማ ብሩ ፥ በአንድ ወቅት ከደብረ ማርቆስ እስከ ባሕርዳር የሚሠሩ የዘይት ኢንዱስትሪዎችን ይጎበኛል። ከዚያ ጉብኝት ሲመለስ ግን የኦሮሚያ ክልል አመራርን በመሰብሰብ ተግሣፅ እና ቁጭት ነው ያወራቸው። "አማራ ድምፁን አጥፍቶ እየሠራ ነው፤ እናንተ ምን እያደረጋችሁ ነው? " የሚል ምክርና በቀል መክራቸው።


በነገራችን ላይ የአገራቱ ኢኮኖሚ በዚህ ሰው እና በአብይ አሕመድ ዘረኛ ስሌት እንዲዘወር ተደርጎ ተሠርቷል። ግርማ ብሩ፡ "የብሔራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ምክር ቤት" ሰብሳቢ ነው። ይህ ምክር ቤት ደግሞ ከገንዘብ ሚኒስትሩም ከብሔራዊ ባንክ ገዢዉም በላይ በአገሪቱ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ስልጣን ያለው ነው። በሌላ መድረክ ደግሞ፡ ልማደኛው ሽመልስ አብዲሳ፡ ለወገኖቹ መነቃቃት ሲሠራ ፡ "ሺ በላይነህ ክንዴዎችን እንፈጥራለን" በማለት፥ የንፅፅር እና ፉክክር ግቡ ከአማራ ባለሀብት ጋር መሆኑን አሰቀመጠ።


በአንድ ወቅት የአማራ እና ኦሮሞ ባለሀብቶች፡ ፊት ለፊት ተገናኝተው የመወያየት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር። በዩኒቨርሲቲዎች ያለውን የተማሪዎች ግድያ በተመለከተ መፍትሔ ፍለጋ ተብሎ የተጀመረ ማጭበርበራያ መደረክ ነበር። ያ መድረክ ግን የኦሮሞ ልሒቃን ፡ የኢኮኖሚ ጄኖሳይድ ከፖለቲከኞች አልፎ የቢዝነስ ልሒቃን አላማ መሆኑን የገለጠ ነበር። የሁለቱ ሕዝብ ባለሀብቶች፡ ስለአገር ሰላም ሊመክሩ ቢሰባሰቡም ፥ የኦሮሞ ልሒቃን ግን የፖለቲካውን ኢኮኖሚያዊ ትርክት ይዘው ቀረቡ ። "ኢኮኖሚያችንን ይዛችሁታል፣ ወጪና ገቢ ንግድ ተቆጣጥራችሁታል፣ የኦሮሚያ ከተሞችን አማራ

ይዟቸዋል፣ የከተሞች ሀብት በአማራ የተያዘ ነው ..." ወዘተ በማለት ቅናት ይሉት ምቀኝነት አወረዱባቸው። ይሔ "ሁሉን ነገር ይዛችሁብናል" የሚለው የኦሮሞ ባለሀብቶች ክስ ለአማራ ባለሀብቶች አስደንጋጭና የማይጠበቅ ንግግር የነበረ ቢሆንም ሁሉንም የሰሙበት መድረክ ነበር።


የጋዜጠኛ መሳይ መኮንን ጥቆማ ጨምረን እናንሳ እና ወደኢኮኖሚያዊ ዘር ማጥፋት ተግባሮቻቸው እንዝለቅ። መሳይ መኮንን በአንድ የማህራዊ ሚድያ ልጥፉ በኢትዮጵያ በነበረበት ወቅት ስሙን መጥቀስ ካልፈለገው ጀነራል ጋር አደረኩት ያለው ውይይት ጥቆማው የምናወራውን ፀረ-አማራ የኢኮኖሚያዊ ዘር ማጥፋት አላማ ጠቋሚ ነው። በእርግጥ ጀነራሉ ብርሃኑ ጁላ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም። በውይይታቸው የተነሱት የጎጃም አማራ ባለሀብቶች ናቸው።


መሣይ እንዲህ ይላል ፥

" ከአንድ የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አዛዥ ጋር እየተጨዋወትን ነው። በመሀል አንድ ርዕሰ ጉዳይ ተነሳ። ስለአማራ ተወላጅ ባለሀብቶች። አዛዡ 'የኢትዮጵያ የወቅቱ ችግር ምንጭ የአማራ ባለሀብቶችና ምሁራን ናቸው' የሚል ግልብ ሀሳብ ዱብ አደረጉብኝ። እውነት ለመናገር ደንግጬአለሁ። በእሳቸው ደረጃ እንዳዚያ ዓይነት ቦልድ አቋም አልጠበኩም ነበር። ዝም ብዬ ማዳመጤን ቀጠልኩ። 'ስታር ቢዝነስ ግሩፕ የሚባል የአማራዎች ድርጅት ካወክ ዋና ስራቸው ይሄን መንግስት ለመገልበጥ የሚደረግን እንቅስቃሴ ከጀርባ መደገፍ ነው። በደንብ ደርሰንበታል። እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ባለሀብቶችም ከማን ጀርባ እንዳሉ እናውቃለን። ከመንግስት የሚመጣውን ትዕዛዝ እየጠበቅን ነው እንጂ ልክ እናስገባቸዋለን' እያሉ ቀጠሉ።"


ጋዜጠኛ መሳይ በውጥረት ስሜት ሆኜ አንድ ጥያቄ አነሳሁላቸው ይላል። ''ጦርነቱን መንግስት በአሸናፊነት እንዲያጠናቅቅ የአማራ ባለሀብቶች የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ እኮ ነው። ለአብነትም...' ብዬ እነበላይነህ ክንዴንና ወርቁ አይተነውን ጠቀስኩላቸው።"


የጀነራሉን መልስ ያስከትላል።


"ፊት ለፊቴ የተቀመጡት አዛዥ ግን ሀሳቤ የጣማቸው አይመስሉም። የፊታቸው ገጽታ በአነጋገሬ የተደሰቱ እንዳልሆኑ የሚያሳብቅ ነው።

'ተዋቸው። እነሱም ቢሆኑ አጥር ላይ የተንጠለጠሉ እንጂ ወዴየትኛው እንደተሰለፉ እርግጠኛ አይደለንም።' በእውነቱ ግራ ገባኝ። ምን እየተደረገ ነው? ወዴት እየሄድን ነው? በየቴሌቪዥኑ መስኮትና በየመድረኩ የሚስተጋባው ፕሮፖጋናዳ ሌላ ነው። ሰዎቹ በውስጣቸው የሚንተከተከው ግን ከወዲህ ነው።"


አዎ!

ከወዲህ ያለው ጉዳይ የኢኮኖሚ ዘር ማጥፋት ነው።


ፋሽስታዊው ልሒቅ በ2008/2009 አ.ም የለውጥ ዋዜማ እንቅስቃሴ ወቅት በእነጃዋር መሐመድ መሪነት በክልሉ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፋብሪካዎች ሲወድሙ ፣ ኢንቨስትመንቶች ሲቃጠሉ የማሕበራዊ ንቅናቄ አካል የሆነ ትግል እንጂ የኢኮኖሚ ጥፋት አላማ አድርጎ የተመለከተው ብዙም አልነበረም። በርግጥ ዛሬ ስልጣን የያዘው ቡድን ያኔ ይዟቸው ብቅ ካላቸለው ጉዳዮች መካከል፣ "የኦሮሚያ የኢኮኖሚ አቢዮት" የሚል ነበር።


ያኔ ጀመርነው ያሉት የልማት ዘመቻ ከወያኔ ጋር መፎካከርን መነሻ ያደረገ እና ከተሠራም በክልሉ ውስጥ በሚሠራ ሥራ መፈፀምን የሚጠይቅ ስለነበር በዚያው የቀረና ከስልጣን ቁጥጥር በኋላ መልኩን ቀጥሎ የመጣ ነው። ነገሩ ገና ሲጀመር በለማ መገርሳ መሪነት "ኦሮሚያ" ባሉት ግዛት ውስጥ ያሉ ኢንቨስተሮችን "ቄሮን ቅጠር ወይ ውጣ" አይነት አስገዳጅና ገፊ ቢሮክራሲ በመትከል ባለሀብቶችን የማስገደድ ሥራ ውስጥ ነበር የገቡት። ከእነዳንጎቴ ስሚንቶ ጀምሮ፣ እነ አይካአዲስ ጨርቃጨርቅ ሌሎች ባለሀብቶች የምርት ሥራ ለመስራት ከፈለጉ፥ ቢሠራም ባይሠራም የኦሮሞን ቄሮ መቅጠር ግዴታ ከማድረግ ጀምረው፡ ትላልቆቹ ሌቦች ደግሞ በምርት ማከፋፈልና መሠል ሥራ ብቸኛ ቁጥጥር ለመውሰድ አስገድደዋል።


እነሜድሮክን ጨምሮ ትላልቅ ኢንቨስትመንት ውስጥ ያሉ ባለሀብቶች ቄሮ ንብረታችሁን እንዳያቃጥል ይሔንን ያሕል ክፈሉ ይባሉ ነበር። እንደሚድሮክ ወርቅ ያሉትን ደግሞ መሥራት ከፈለጋችሁ ይሔንን ያሕል ክፈሉ የሚል ግዙፍ ድርድር ተጥሎባቸው ነበር።


ሽመልስ እንዳለው የፌዴራል መንግስቱን መቆጣጠር ከልክ በላይ ለመዝረፍም እድል ከፍቷልና ነው።


የዘራፊው ቡድን የስልጣን ቁጥጥሩን ሲያረጋግጥ በቀዳሚነት ያደረገው የአገሪቱን የፋይናንስ ተቋማት መቆጣጠር ነው። የአገሪቱ ትልቁ አበዳሪ ተቋም የሆነውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፥ ባጫ ጊና የተባለ ሰው በመሾም ተቋሙንም፣ ገንዘቡንም መዘበሩት።


ሪፖርተር ጋዜጣ ያወጣው አንድ ዘገባ ላይ የተቋሙን ቁጥጥር ሥራ እንደሚከተለው ፅፎት ነበር።


" በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በከፍተኛው የማኔጅመንት ዕርከን ሲያገለግሉ ከነበሩ ስምንት ምክትል ፕሬዚዳንቶች ሰባቱ ባንኩን ለቀቁ፡፡ ንግድ ባንክን እንዲመሩ የተሾሙት አዲሱ ፕሬዚዳንት አቶ ባጫ ጊና ኃላፊነታቸውን ከተረከቡ ወዲህ ከበታች የነበሩ ኃላፊዎች በራሳቸው ፈቃድ ባንኩን ስለመልቀቃቸው የሚገልጹ መረጃዎች ሲመጡ ሰንብተዋል፡፡ ለቀዋል በተባሉት ከፍተኛ የማኔጅመንት አባላት ምትክም አዳዲስ አመራሮች ተሹመዋል፡፡ ስምንት የስራ ሃላፊዎች ደግሞ ከአዋሽ ባንክ ወደ ንግድ ባንኩ እንዲዛወሩ ተደርጓል።"

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአቶ ባጫ ጊና አመራር ዘመን እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ በብድር መልክ እና በተበላሸ ብድር ስም ወጥቶ እንዲቀር ተደርጓል።


ስልጣን በያዙ በአመቱ የባንኩ ትርፍ በ10.3 በመቶ ቀንሶ ነበር። አንድ የዋዜማ ራዲዮ ዘገባ እንደተጠቀሰው በወቅቱ "ባንኩ በገባበት ችግር ምክንያት ለሰራተኞቹ ይሰጥ የነበረውን የቤትና የመኪና ብድር ለማቆም ተገዷል። የአሁኑ የንግድ ባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ የተቋሙን ችግር ለመፍታት እየሰሩ እንደሆነ እየተነገረላቸው ነው።" በማለት ዘግቦ ነበር።


ልክ እንደንግድ ባንክ ሁሉ የገቢዎችና ጉምሩክ ሥርዓቱን ሌላውን መምቻና በአንድ ቡድን ቁጥጥር መፈንጫ እንዲሆን ለማድረግ የዛሬዋ የአዲስአበባ ከንቲባ በተሾመችበት ዘመን መነጋገሪያ የሆኑ የሠራተኛ ቅጥር ሥራዎችን በማድረግ እንደወረራ የሚቆጠር ሥራ ፈፅመውበታል። ባለሀብት እየተለየ በግብር ማስፈራሪያ እና ዛቻ መመዝበር እንዳለ ሆኖ ፥ የራስ ወገን ያሉትን በግብር እና ጉምሩክ ጥቅማጥቅሞች መድሎ መሥራት የገዢው ቡድን ኢኮኖሚያዊ ሴሬ አካል ሆኖ ብዙ

ጉዳይ ተፈፅሟል። ሥርዓቱን ይዘነዋል ሲባልም እንደዚህ ባሉ ጉዳዮች የአገሪቱን ፋይናንስ፣ ጉምሩክና ቀረጥ ተመን፣ የመንግስት ግዢና የጨረታ ሥራ ወዘተ ተወርቶ የማያልቅ ግፎችን ፈፅመዋል እየፈፀሙ ነው።

ይሔ እና ሌሎች ሰፊ የኢኮኖሚ ዘር ማጥፋት አላማዎችን ሲፈፅሙ ፣ ለእነሱ "ከልክ በላይ ማደግን እያሠቡ ለሌላው ከልክ በላይ መውደቅን" ሲያሴሩ ፡ ትልቁ አላማቸው የኢትዮጵያን እና አፍሪካን ትልቅ የአገር ውስጥ ምርት ምንጭ ኦሮሚያን እናደርጋለን ከሚል ስሌት ነው።

ሁሌም ነገር የማይደብቀን ሽመልስ አብዲሳ ተከታዩን ሀሳብ በማስቀመጥ ጥሎ የመቆም ምኞቱን አኑሯል።

"በመጪዎቹ 30 እና 40 አመታት የኢትዮጵያ ንግድ የሚባለው ፣ የኢትዮጵያ ጂዲፒ የሚባለው ሸገር ፣ ቢሾፍቱ፣ የገዳ ስፔሻል የኢኮኖሚክ ዞን እና አዳማ ይሆናሉ። ገዳ ስፔሻል የኢኮኖሚ ዞን የአፍሪካ ቁጥር አንድ ጂዲፒ እንደሚሆን አንዳች ጥርጣሬ የለኝም። ይሔም በቀጣዩቹ 30 እና 40 አመታት እውን የሚሆን ነው "

ስልታዊ የአማራን እና የባለሀብቱን አቅም የማዳከም ሴራ ፣ በጦርነት አማራውን ማድቀቅ እንደኢኮኖሚ ጥቃት ስልት እንዲሁም በተለያየ መንገድ ከኢኮኖሚውና ከሥራ እየተወገደ ስላለው አማራ በቀጣይ ክፍል 2 ዝግጅታችን እንቃኛለን።

ጤና ይስጥልን!!




 

Disclaimer: The opinions expressed in this article are those of the authors. They do not purport to reflect the opinions or views of the Amhara Popular Front ( APF) or its affiliates.

12 views0 comments

Comments


bottom of page